ባሕር ዳር:ሚያዝያ 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍጻሜ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ አርሰናል “የውድድሩ ንጉስ” ማድሪድን 3ለ0 አሸንፏል። የመልሱ ጨዋታ ለብዙዎቹ ከጉጉት የተነሳ ሳምንቱ ቢረዝም፣ አሁን ቀጠሮው ዛሬ ለመባል ደርሷል። ሪያል ማድሪድ በሻምፒዮንስ ሊግ 15 ዋንጫዎችን የሠበሠበ ሲኾን ይህም ከየተኛውም ክለብ በላይ የሚያስቀምጠው ታሪኩ ነው።
በአርሰናል በኩል ደግሞ የሚነገረው ተቃራኒው ነው። ቡድኑ በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ጥሩ ታሪክ የጻፈ እና አዝናኝ እግር ኳስን በመጫወት ብዙ ደጋፊዎች ያሉት ቢኾንም በሻምፒዮንስ ሊጉ ግን ክብሩን የሚመጥን ታሪክ የለውም። ዋንጫውን የመፈለግ ጉዞው እስካኹንም አልሠመረም።
የእንግሊዙ ክለብ ዘንድሮም ለሻምፒዮንስ ሊጉ ዋንጫ ያጨው ባይኖርም ሳምንት ማድሪድን የረታበት መንገድ እና ዛሬ የቤርናቦውን ፈተና መቋቋም ከቻለ ለዋንጫ ግምት ያገኛል።
በኤምሬትሱ ጨዋታ በደክላን ራይስ መንታ በሚመስሉ ግቦች የፈራረሰው ሪያል ማድሪድ የ3ለ0 ውጤትን መቀልበስ ቀላል ባይኾንም ዛሬ በብዙ አርሰናልን ይፈትናል። ካርሎ አንቾሎቲ ከለንደኑ ሽንፈት በኋላ ሳምንት ሁሉ ነገር ይቀየራል የሚል ሀሳብ ሰጥተው ነበር። በብሔራዊ ቡድን አጋሩ ራይስ ቅጣት ምቶች መገረሙን ያልደበቀው ቤልንግሃምም በማድሪድ የማይቻል ነገር የለም ውጤቱን እንቀለብሳለን ብሏል።
የአርሰናሉ ግብ ጠበቂ ዴቪድ ራያ ደግሞ የራሳችንን ታሪክ ለመጻፍ ማድሪድ ተገኝተናል፤ የሚሰማን ፍርሀት ሳይኾን በራስ መተማመን ነው ያለው። ከሁለቱ ክለቦች ውጭ ያሉ ሰዎችም በዚህ ጨዋታ ዙሪያ የተለያየ ሀሳብ አላቸው። አርሰናል ደስታውን ሳምንት ሙሉ አጣጥሟል አሁን ተራው የነጮቹ ነው።
ምባፔ፣ ቪንሽየስ እና ቤሊንግሃምን ማቆም ይከብደዋል እና የሚሉት በአንድ፤ አርሰናል ትልቁን ሥራ ሠርቷል፣ ቀሪው ውጤት ማስጠበቅ ነው ይሄ ለአርሰናል ቀላል ነው ባዮች ደግሞ በሌላ። የዚህኛው ሀሳብ ማጠናከሪያ አርሰናል በማጥቃት እንጅ ድክመቱ በመከላከል ድንቅ መኾኑ በዋናት ይነሳል።
በብዙዎች የሚፈራው ሪያልማድሪድ አርሰናል ላይ እጁን የሚሰጥበት ታሪኩም ለእንግሊዙ ክለብ ደጋፊዎች ሌላ ስንቅ ነው። ሁለቱ ክለቦች ከዚህ በፊት በሦስት አጋጣሚ ተገናኝተው ሁለቱን መድፈኞቹ አሸንፈዋል፤ ቀሪው አቻ የተጠናቀቀ ጨዋታ ነው። ስለዚህ የዛሬው ጨዋታም ጥቁር ታሪክን የመፉቅ እና የበላይነትን ለማስቀጠል ጭምር የሚደረግ ትግል ይኾናል።
በእነዚህ እና ሌሎች ምክንያቶች በብዙዎች የተናፈቀው ጨዋታ ምሽት 4:00 ቤርናቦኦ ላይ ይጀምራል። እስከዚያው ግን ጭንቀቱም፣ ቁጭቱም ይቀጥላል። ከጨዋታው ጋር የተያያዙ እውነታቸው፦
-ሪያል ማድሪድ በአውሮፓ መድረክ በመጀመሪያ ዙር ሦስት እና በላይ ግብ ተቆጥሮበት አምስት ጊዜ ተሸንፏል። በሁለት አጋጣሚ በመልስ ጨዋታ ውጤት ቀልብሷል።
-የስፔኑ ክለብ በአውሮፓ መድረክ በሜዳው 53 ጊዜ ከእንግሊዝ ክለቦች ጋር ተጫውቶ በሁለት ጨዋታ ብቻ ከሦስት በላይ ግብ አስቆጥሮ አሸንፏል።
-ከ2015/16 ወዲህ ማድሪድ በሻምፒዮንስ ሊግ 16 የመልስ ጨዋታዎችን አድርጎ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ ያልቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው።
-አርሰናል የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ ከ2009 በኋላ ለግማሽ ፍጻሜ ሲደርስ ለመጀመሪያ ጊዜ ይኾናል።
-አርሰናል በዚህ ዓመት በሻምፒዮንስ ሊጉ 28 ግቦችን አስቆጥሯል፤ የተቆጠሩበት ደግሞ ስድስት ብቻ ናቸው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን