በኢትዮጵያ ፕሪምዬር ሊግ ፋሲል ከነማ ከኢትዮጵያ ቡና የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።

0
128

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በ25ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምዬር ሊግ ዛሬ ፋሲል ከነማ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።

ባለፉት ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ድል ቀንቷቸው በጥሩ ተነሳሽነት ላይ የሚገኙት ፋሲል ከነማዎች ዛሬም ተከታታይ ድላቸውን ለማስቀጠል ይፋለማሉ።

አጼዎቹ ባለፉት ጨዋታዎች ቅዱስ ጊዮርጊስን 2ለ1፣ ወልዋሎ አዲግራትን 2ለ1፣ መቻልን 4ለ2 በኾነ ውጤት በመርታት ጥንካሬአቸውን አሳይተዋል።

በተለይም የአጥቂው ጌታነህ ከበደ ወደ ግብ አስቆጣሪነት መመለስ ቡድኑን ባለፉት ጨዋታዎች ሳይሸነፍ እንዲቀጥል አስችለውታል።

በተቃራኒው ኢትዮጵያ ቡና ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች የተረጋጋ አቋም አላሳየም። ባለፉት ሥስት ጨዋታዎች በአንደኛው ተሸንፏል፣ በአንደኛው አቻ ወጥቷል። በአንደኛው ደግሞ አሸንፏል።

ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በፕሪምየር ሊጉ 16 ጊዜ ተገናኝተዋል። ከዚህም ውስጥ ፋሲል ከነማ ስድስት ጊዜ ሲያሸንፍ ኢትዮጵያ ቡና አራት ጊዜ አሸንፏል። ቀሪዎቹ ስድስት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ነው የተጠናቀቁት።

እስካሁን ባለው የጨዋታ ታሪክ ፋሲል ከነማ የበላይነት ያለው ቢኾንም የዛሬው ጨዋታ በሁለቱም ቡድኖች ከፍተኛ ፉክክር እንደሚታይበት ይጠበቃል።

የፋሲል ከነማ አጥቂዎች በጥሩ ብቃት ላይ መገኘታቸው የዛሬውን ጨዋታ ተጠባቂ እንዲኾን አድርጎታል።

የአጼዎቹ ተከታታይ ድል ይቀጥላል ወይስ ቡናዎች ይህንን ጉዞ ይገቱታል? የሚለው ተጠባቂ ነው። ጨዋታው ቀን 9:00 ይደረጋል።

በሌላ ጨዋታ መቻል ከአርባምንጭ ከተማ ይጫወታሉ። ጨዋታው ምሽት 12:00 ላይ ይደረጋል።

የኢትዮጵያ ፕሪምዬር ሊግን የደረጃ ሠንጠረዥ ኢትዮጵያ መድን በ45 ነጥብ ሲመራው ባሕር ዳር ከተማ እና ወላይታ ዲቻ በ37 ነጥብ በጎል ክፍያ ተበላልጠው 2ኛ እና 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

በምሥጋናው ብርሃኔ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here