ውድድሩ አንድነትን እና አብሮነትን ከማሳየትም በላይ የዞኑን ስፖርት ያነቃቃ እንደነበር የወጣት እና ስፖርት ቢሮ ኀላፊ እርዚቅ ኢሳ ገለጹ።

0
112

ደሴ:ሚያዝያ 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከመጋቢት 26/2017 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው የ9ኛው መላው ደቡብ ወሎ ዞን ስፖርታዊ ውድድር ዛሬ ሲጠናቀቅ በፍጻሜ በተደረጉ ጨዋታዎች በወንዶች መረብ ኳስ ለገሂዳ ወረዳ መቅደላ ወረዳን 3ለ2 በማሸነፍ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ኾኗል።

በእግር ኳስ የፍጻሜ ጨዋታ ደግሞ ቃሉ ወረዳ ሃርቡ ከተማን በመለያ ምት 3ለ1 አሸንፏል። በአጠቃላይ በፓራሊምፒክ እና መስማት በተሳናቸው ደላንታ ወረዳ አሸናፊ ሲኾን በኦሎምፒክ ስፖርት ደግሞ ተንታ ወረዳ አሸናፊ ኾኗል። ውድድሩ የእርስበርስ ግንኙነትን በማጠናከር ተነፋፍቆ የነበረውን የስፖርት ቤተሰብ ያገናኘ እንደነበር ተሳታፊዎች ገልጸዋል።

በቆይታቸው ለተደረገላቸው መልካም መስተንግዶም ምሥጋና አቅርበዋል። የደቡብ ወሎ ዞን ወጣት እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ጀማል ሞላ በውድድሩ 23 ወረዳ እና ከተማ አሥተዳደሮች መሳተፋቸውን ገልጸዋል። ውድድሩ ከጅማሬው እስከ ፍጻሜው እጅግ ሰላማዊ ኾኖ መጠናቀቁንም ነው የተናገሩት።

ዝግጅቱ የስፖርት ቤተሰቡን ከናፈቀው ውድድር ጋር ማገናኘቱን የጠቀሱት ኀላፊው በቀጣይ በመላው አማራ በሚካሄደው ውድድርም ላይ የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ ይሠራል ብለዋል። የአማራ ክልል ወጣት እና ስፖርት ቢሮ ኀላፊ እርዚቅ ኢሳ ውድድሩ አንድነትን እና አብሮነትን ከማሳየትም በላይ የዞኑን ስፖርት ያነቃቃ እንደነበር ገልጸዋል።

ውድድሩ የተሳካ ኾኖ እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላትም ምሥጋና አቅርበዋል። ከሚያዚያ 19/2017 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ የመላው አማራ ውድድር በደሴ ከተማ አዘጋጅነት እንደሚቀጥልም ጠቅሰዋል።

ዘጋቢ፦ ተመስገን አሰፋ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here