ተጠባቂ ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ።

0
173

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በቀጣዩ ሳምንት ከሪያል ማድሪድ ጋር ለሚደርገው የቻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍፃሜ ሁለተኛ ዙር የደርሶ መልስ ጨዋታ ዝግጅት ላይ የሚገኘው አርሰናል በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ በሜዳው ብሬንትፎርድን ያስተናግዳል። የአርሰናሉ አሠልጣኝ ሚኬል አርቴታ ከባድ ጨዋታ ከፊታቸው በመኖሩ የተወሰኑ ተጫዋቾቻቸውን ሊያሳርፉ ይችላሉ ተብሎ ነው የሚጠበቀው።

በተለይም ቡካዮ ሳካ እና ዴክላን ራይስ በሳምንቱ አጋማሽ ከሪያል ማድሪድ ጋር በነበረው ጨዋታ ላይ ትንሽ ጉዳት አስተናግደው በመውጣታቸው አሠልጣኙ በዚህ ጨዋታ ሊያሳርፏቸው ይችላሉ የሚል ግምት አለ። በተቃራኒው የብሬንትፎርዱ አሠልጣኝ ቶማስ ፍራንክ ቡድናቸው ምንም አዲስ የጉዳት ችግር እንደሌለበት አስታውቀዋል። ኾኖም ፋቢዮ ካርቫልሆ፣ ጆሹዋ ዳሲልቫ፣ ኢጎር ቲያጎ፣ አሮን ሂኪ እና ጉስታቮ ኑንስ አሁንም ከጉዳት አላገገሙም።

አርሰናል ከብሬንትፎርድ ጋር ያደረጋቸውን አራት ጨዋታዎች አሸንፏል። በአጠቃላይ ሲታይ አስር ያክል በሜዳው ያደረጋቸውን ጨዋታዎች ከአንድ ጊዜ በስተቀር በብሬንትፎርድ አልተሸነፈም። ብሬንትፎርዶች በፕሪሚየር ሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ ባደረጉት ጨዋታ አርሰናልን ቢያሸንፉም ከዚያ በኋላ ግን ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ አልቻሉም።

አርሰናል በሜዳቸው በተደረጉ የለንደን ደርቢዎችም በጣም ጠንካራ አቋም ያሳየ ሲኾን ካለፉት አስራ አምስት ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ብቻ ነው የተሸነፈው። በሌላ በኩል ብሬንትፎርድ በቅርብ ጊዜ ጥሩ ውጤት እያሳየ አይደለም። ብሬንትፎርዶች ከሜዳቸው ውጭ በተደረጉ ጨዋታዎች ግን የተሻለ ብቃት አሳይተዋል። በዚህ የውድድር ዓመት ከሜዳቸው ውጭ ባደረጓቸው ጨዋታዎች ሁሉ ጎል ማስቆጠርም ችለዋል።

አርሰናል ምንም እንኳን ወሳኝ የቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ከፊቱ ቢጠብቀውም በሜዳው ብሬንትፎርድን የማሸነፍ ዕድሉ ከፍተኛ ስለመኾኑ ነው እየተነገረ የሚገኘው። አሠልጣኙ አርቴታ የተወሰኑ ተጫዋቾቹን ቢያሳርፉም ቡድኑ በቂ የተጫዋቾች ሥብሥብ ያለው በመኾኑ ጨዋታውን በድል ሊያጠናቅቅ ይችላል ተብሎ ነው የሚጠበቀው።

ዛሬ አርሰናል በሚያደርገው ጨዋታ በ62 ነጥብ ሁለተኛ ያለውን ደረጃ ለማጠናከር በሜዳው ጨዋታውን ያደርጋል። ፕሪሚየርሊጉን ሊቨርፑል በ73 ነጥብ እየመራው ነው የሚገኘው። ጨዋታውም ምሽት 1 ሰዓት ከ30 የሚካሄድ ይኾናል።

በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ሌሎች ጨዋታዎች የሚካሄዱ ሲኾን በተለይም ማንቸስተር ሲቲ ክሪስታል ፓላስን በሜዳው የሚያስተናግድበት ጨዋታ ተጠባቂ ነው። ይህ ጨዋታ ለማንቸስተር ሲቲ ወሳኝ ሲኾን አሁን ካለበት በ52 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ወደ አራተኛ ደረጃ ከፍ የሚልበት በመኾኑ ጨዋታውን ትኩረት ሰጥቶ ለማሸነፍ ወደ ሜዳ የሚገባ ይኾናል።

ማንችስተር ሲቲ አሁንም ቁልፍ ተጫዋቾቻቸውን ማለትም ማኑዌል አካንጂን፣ ናታን አኬን፣ ኤርሊንግ ሃላንድን፣ ሮድሪን እና ጆን ስቶንስን ሳይዙ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። እነዚህ ተጫዋቾች በጉዳት ምክንያት ከሜዳ ርቀው የሚገኙ ቢኾንም አሠልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ ግን የጉዳት ሁኔታው እንደማያስጨንቃቸው ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ክሪስታል ፓላስ ከባድ ፈተና ይጠብቀዋል። ባለፈው ሳምንት ከብራይተን ጋር በነበራቸው ጨዋታ ቀይ ካርድ የተመለከቱት ማርክ ጉሄ እና ኤዲ ንኬትያ በዚህ ጨዋታ ላይ አይሰለፉም። ይህ ቡድኑን በተከላካይ እና በአጥቂ ክፍሎች ላይ ክፍተት ይፈጥርበታል። ኾኖም ተከላካዮቹ ማክሴንስ ላክሮክስ እና ክሪስ ሪቻርድስ ከጉዳታቸው አገግመው ለጨዋታው ዝግጁ መኾናቸው በመልካም ታይቷል። ቻዲ ሪያድ እና ቼክ ዱኩሬ ግን አሁንም በረጅም ጊዜ ጉዳት ምክንያት ከሥብሥቡ ውጭ ናቸው። ጨዋታውም ቀን 8 ሰዓት ከ30 ነው የሚካሄደው።

በፕሪምየር ሊጉ ሌሎች ጨዋታዎችም ሲካሄዱ ብራይተን ሆቭ አልቢዮን ሌስተር ሲቲን የሚያስተናግድ ሲኾን ኖቲንግሃም ፎረስት ከኤቨርተን ጋር ይጫወታል። በሌላ ጨዋታ ደግሞ ሳውዝሃምፕተን እና አስቶን ቪላ ወሳኝ ጨዋታዎችን ያደርጋሉ። እነዚህ ጨዋታዎች በተመሳሳይ 11 ሰዓት ይካሄዳሉ።

በምሥጋናው ብርሃኔ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here