የአፍሪካ ዋንጫ ዛሬ ሲቀጥል ምድብ አንድና ሁለት ላይ የሚገኙ ቡድኖች ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

0
251

ባሕርዳር: ጥር 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በምድብ አንድ ኢኳቶሪያል ጊኒ ከኮትዲቯር እና ጊኒ ቢሳው ከናይጀሪያ ሲገናኙ፤ ምድብ ሁለት ላይ ደግሞ ኬፕ ቨርዴ ከግብጽ እና ሞዛምቢክ ከጋና ይጫወታሉ።

ኢኳቶሪያል ጊኒ ባደረገቻቸው 11 የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ጨዋታዎች የተሸነፈችው በሁለቱ ብቻ ነው፡፡ በስደስት ጨዋታዎች አሸንፋለች፤ በሦስት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ወጥታለች፡፡
በዚህ የአፍሪካ ዋንጫ ኢኳቶሪያል ጊኒ ሁለት ጨዋታዎችን አድርጋ በአንዱ በማሸነፍ እና በአንዱ አቻ በመለያየት ምድቡን በአራት ነጥብ እየመራች ትገኛለች፡፡

ኮትዲቯርም ሁለት ጨዋታዎችን አድርጋ በአንዱ ረትታ እና በሌላው ተሸንፋ በሦስት ነጥብ 3ኛ ደረጃን ይዛለች። ናይጀሪያ ደግሞ በአንድ ጨዋታ አሸንፋ እና በአንዱ አቻ ተለያይታ በአራት ነጥብ ሁለተኛ ናት፡፡ በመኾኑም ዛሬ ኢኳቶሪያል ጊኒ ከኮትዲቯር የሚያደርጉት ጨዋታ ወሳኝ ነው፡፡ ጨዋታውን የሚያሸንፈው ሀገር የምድቡ መሪ ይኾናል።
በአንጻሩ አቻ መውጣት ለኢኳቶሪያል ጊኒ ሲጠቅማት ኮትዲቯርን ግን አጣብቂኝ ውስጥ እንድትገባ ያደርጋታል፡፡

በዚሁ ምድብ”ሀ” የሚገኙት ጊኒ ቢሳው ከናይጀሪያ በፌሊክስ ቦኚ ስታዲያም ምሽት 2 ሰዓት ይጫወታሉ፡፡

ሁለቱ ሀገራት በአፍሪካ ዋንጫ ሲገናኙ ለሁለተኛ ጊዜ ነው ፡፡ ጊኒ ቢሳው እና ናይጄሪያ በሦስት ተከታታይ የአፍሪካ ዋንጫ በተመሳሳይ ምድብ ውስጥ ተገናኝተዋል፡፡ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2022 ከምድባቸው ናይጄሪያ በበላይነት አጠናቅቃለች፡፡ 2023 የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታም ናይጄሪያ የበላይ ስትሆን ጊኒ ቢሳው ሁለተኛነት አጠናቅቃለች፡፡

ጊኒ ቢሳው ባደረገቻቸው ያለፉትን አራት ተከታታይ ጨዋታዎች ተሸንፋለች። ይህም ቡድኑን ደካማነት ያሳያል፡፡

በአንጻሩ ናይጄሪያ ካለፉት 12 የአፍሪካ ዋንጫዎች ውስጥ 10 ጨዋታዎችን አሸንፋለች፤ በአንዱ አቻ ተለያይታለች፡፡ ይህም የንስሮችን ጠንካራነት ያመላከተ ነው፡፡ በመኾኑም የዛሬውን ጨዋታ በቀላሉ ትረታለች ሲል ዴይሊ ሜይል ስፖርት ዘግቧል፡፡

በዚህ የአፍሪካ ዋንጫ ናይጀሪያ በአራት ነጥብ እና በአንድ የንጹህ ግብ ክፍያ በሁለተኛነት ተቀምጣለች፡፡ ይህን ጨዋታ ካሸነፈች ደግሞ ሰባት በማድረስ የምድቡ መሪ ትኾናለች፡፡ በአንጻሩ ጊኒ ቢሳው ያደረገችውን ሁለት ጨዋታዎች በመሸነፍ በደረጃ ሰንጠረዡ ያለምንም ነጥብ መጨረሻ ላይ ትገኛለች፡፡

በኦፕታ ሱፐር ኮምፒውተር ቅድመ ትንበያ መሰረት ናይጄሪያ 61 ነጥብ 2 በመቶ ጨዋታውን ታሸንፋለች፡፡

በምድብ”ለ” ኬፕ ቨርዴ ከግብጽ በፌሊክስ ቦኚ ስታዲያም ምሽት 5 ሰዓት ይጫወታሉ፡፡

የሰባት ጊዜ ሻምፒዮናዋ ግብጽ ኬፕ ቨርዴን ስትገጥም ይህ የመጀመሪያው ግጥሚያቸው ይኾናል።

ኬፕ ቨርድ በ34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ያደረገቻቸውን ሁለት ጨዋታዎች አሸንፋ ምድቡን በሰድስት ነጥብ እየመራችው ትገኛለች፡፡

ግብጽ በሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይታለች፡፡ በሁለቱ ጨዋታዎችም አራት ግቦችን አስተናግዳለች፡፡ በመኾኑም ያላት ነጥብ ሁለት ብቻ ነው፡፡ ስካይ ስፖርት በድረ ገጹ ” በ34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የግብጽ ብሔራዊ ቡድን ደካማ እንቅስቃሴ አድርጓል” ሲል አስነብቧል፡፡

በሌላ በኩል በምድብ “ሀ” የሚገኙት ሞዛምቢክና ጋና ያላቸው ነጥብ አንድ አንድ ብቻ በመኾኑ ግብጽ በሁለት ነጥብ ከምድቧ በሁለተኛነት እንድትቀመጥ አድርጓታል፡፡

ግብጽ በኬፕ ቨርዴ ከተሸነፈች ወይም ሁለቱ ቡድኖች አቻ ከተለያዩ እና ሞዛምቢክና ጋና ከተሸናነፉ አሸናፊው ሀገር ግብጽን ከኋላው አስከትሎ በሁለተኛነት ይቀመጣል፡፡

በኦፕታ ሱፐር ኮምፒውተር ቅድመ ትንበያ መሰረት የሰባት ጊዜ ሻምፒዮናዋ ግብጽ 62 ነጥብ 5 በመቶ የማሸነፍ እድል ተሰጥቷታል፡፡

የግብጽ እግር ኳስ ፌደሬሽን ባወጣው መግለጫ “የህክምና ምርመራ ውጤቱ እንደሚያሳየው ሙሐመድ ሳላህን የጡንቻ ጉዳት እንዳጋጠመው ስላረጋገጠ በሁለት የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎች አይሰለፍም” ብሏል።

በምድብ “ለ” ሞዛምቢክ እና ጋና አቢጃን ከተማ በሚገኘው በስታዲ ኦሊምፒክ አላሳን ኦውታራ ስታዲየም 11 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ፡፡ ሁለቱ ሀገራት በአፍሪካ ዋንጫ ሲገናኙ የዛሬው ለሁለተኛ ጊዜ መኾኑ ነው፡፡

የሞዛምቢክ ተናዳፊ እባቦች ባለፉት አራት የአፍሪካ ዋንጫ የመጨረሻ የምድብ ጨዋታዎችን በግብፅ፣ በጋና፣ በዛምቢያ እና በናይጄሪያ ተሸንፋለች። ቡድኑ በ34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ሁለት ጨዋታዎችን አድርጎ በአንዱ አቻ ተለያይቶና በአንዱ ተረትቶ በሦስት የግብ ዕዳ አራተኛ ደረጃን ይዞ ይገኛል።

ጋና ባደረገቻቸው ሁለት የምድብ ጨዋታዎች በአንዱ አቻ ተለያይታለች፤ በአንዱ ደግሞ ተረትታለች፤ ስለኾነም በአንድ የግብ ዕዳ አንድ ነጥብ ብቻ በመያዝ ሦስተኛ ደረጃን ይዛ ትገኛለች፡፡

በሙሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here