በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ሦስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

0
93

ባሕር ዳር: መጋቢት 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የመጀመሪያው ጨዋታ በወላይታ ድቻ እና በአዳማ ከተማ መካከል 3 ሰዓት ከ30 የሚደረገው ጨዋታ ነው። ይህ ጨዋታ በደረጃ ሠንጠረዡ በ36 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ የሚገኘው እና 20 ነጥብ ይዞ ወራጅ ቀጣና ስጋት ላይ ያለው አዳማ ከተማ የሚያደርጉት ፉክክር ነው።

ወላይታ ድቻ እና አዳማ ከተማ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተደጋጋሚ ሲገናኙ ቆይተዋል። ከዚህ በፊት በተካሄደ ጨዋታ ሁለቱ ቡድኖች 2ለ2 እና 1ለ1 በኾነ አቻ ውጤት ተለያይተዋል። ባለፉት ጨዋታዎች እንደታየው ሁለቱ ቡድኖች ጥሩ ፉክክር ያሳዩ ሲኾን አዳማ ከተማ በቅርቡ 1ለ0 በኾነ ጠባብ ውጤት ማሸነፍ ችሎ ነበር።

በሌሎች ሁለት በተደረጉ ጨዋታዎች ደግሞ ተመሳሳይ የፉክክር መንፈስ የታየ ሲኾን ውጤቶቹም 1ለ1 በኾነ አቻ ውጤት እና 2ለ1 በወላይታ ድቻ አሸናፊነት የተጠናቀቀ ነበር። እስካሁን ባለው ሁኔታ የአዳማ ከተማ ውጤቶች በተወሰነ መልኩ ተለዋዋጭነት ያሳያሉ። አዳማዎች በቅርቡ በደቡብ ኢትዮጵያ ቡና 3ለ1 የተሸነፉ ቢኾንም ከወላይታ ድቻ ጋር ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች 1ለ0 በኾነ ውጤት አሸንፈዋል።

በሌላ በኩል ወላይታ ድቻ ባለፉት ጨዋታዎቻቸው ስምንት ጊዜ አሸንፈዋል። የሁለቱን ቡድኖች የዛሬ ጨዋታም የቡድኖቹን ወቅታዊ አቋም የሚያስመለክተን ይኾናል። በወላይታ ድቻ በኩል ተከላካዩ አዛርያስ አቤል ከህመሙ አገግሞ መመለሱ ሲሰማ የተቀሩት የቡድኑ ተጫዋቾችም ለጨዋታ ዝግጁ መኾናቸው ታውቋል። በአዳማ ከተማ በኩል ግብ ጠባቂው ዳግም ተፈራ ከጉዳት ሲመለስ ቻላቸው መንበሩ ላይሰለፍ ይችላል ነው የተባለው።

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በ33 ነጥብ 7ኛ ደረጃ የሚገኘው ሀዲያ ሆሳዕና እና በ25 ነጥብ 13 ኛ ደረጃ የሚገኘው ድሬዳዋ ከነማ የሚያደርጉት ሌላው የ9 ሰዓት ጨዋታ ነው። ቡድኖቹ በቅርቡ ባደረጓቸው ጨዋታዎች የተለያዩ ውጤቶችን አስመዝግበዋል። ሀዲያ ሆሳዕና በአምስቱ የቅርብ ጊዜ ጨዋታዎቻቸው ከጂማ አባ ጅፋር ጋር ሁለት ጊዜ ያለ ጎል ተለያይተዋል፣ በባሕር ዳር ከነማ 1ለ0 የተሸነፉ ሲኾን ከሲዳማ ቡና ጋር 1ለ1 አቻ ተለያይተዋል። ከዚህ በፊት ግን ጂማ አባ ጅፋርን 1ለ0 አሸንፈዋል።

በሌላ በኩል ድሬዳዋ ከነማ በአምስቱ የቅርብ ጊዜ ጨዋታዎቻቸው አርባምንጭ ከተማን 3ለ1 አሸንፈዋል፣ ከጂማ አባ ጅፋር ጋር ያለ ግብ አቻ ነው የተለያዩት፣ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ አንድ ጊዜ 1ለ0 የተሸነፉ ሲኾን ሌላ ጊዜ ደግሞ 3ለ0 በሜዳቸው ተረተዋል። ከመቐለ 70 እንደርታ ጋርም ያለግብ አቻ ነው የተለያዩት።

በሁለቱ ቡድኖች መካከል በተደረጉት ያለፉ 10 ጨዋታዎች ሀዲያ ሆሳዕና የበላይነት ያለው ሲኾን አምስት ጊዜ አሸንፏል፣ ሁለት ጊዜ አቻ ተለያይተዋል፣ ድሬዳዋ ከነማ ደግሞ ሦስት ጊዜ አሸንፏል። በቅርቡ በተደረገው ጨዋታ ሀዲያ ሆሳዕና ድሬዳዋ ከነማን 3ለ1 በኾነ ውጤት አሸንፏል። ሀዲያ ሆሳዕና በአጠቃላይ በድሬዳዋ ከነማ ላይ የተሻለ የፉክክር ታሪክ ያለው ቢኾንም የቅርብ ጊዜ እንቅስቃሴዎች በተለይም ከድሬዳዋ እና ከአርባምንጭ ጋር ባደረጉት ጨዋታ ያገኙት ድል ቡድኑ የተሻለ ሊኾን እንደሚችል ያሳያል።

በድሬዳዋ ከተማ በኩል መሐመድ ኑር ናስር በጉዳት ሔኖክ ሀሰን በቅጣት አይሰለፉም። በሀድያ ሆሳዕና በኩል ደግሞ መለሰ ሚሻሞ ፣ በረከት ወንድሙ፣ ጫላ ተሺታ አንበሉ ሄኖክ አርፊጮ እና ብሩክ ማርቆስ ከሥብሥቡ ውጭ ናቸው። በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሌላው ጨዋታ 29 ነጥብ ሰብስቦ በ10ኛ ደረጃ የተቀመጠው መቻል እና በ25 ነጥብ 14ኛ ደረጃ ያለው መቀሌ 70 እንደርታ የሚያካሂዱት ጨዋታ ነው።

የመቻል እና የመቀሌ 70 እንደርታ ቡድኖች የቅርብ ጊዜ እንቅስቃሴዎች እንዲሁም ቀደም ሲል ያደረጓቸውን ጨዋታዎች ስንመለከት መቻል በቅርብ ጊዜ ባደረጋቸው ጨዋታዎች ተስፋ አስቆራጭ ውጤቶችን እያስመዘገበ ይገኛል። ቡድኑ ካከናወናቸው አምስት ጨዋታዎች በሦስቱ ላይ ሽንፈትን አስተናግዷል፤ በሁለት ጨዋታ ላይ ደግሞ አቻ ውጤት አስመዝግቧል።

በተለይም በቅርቡ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በ1ለ0 እንዲሁም ከፋሲል ከነማ ጋር 4ለ2 የደረሰባቸው ሽንፈት ቡድኑ በአጥቂ መስመሩ ላይ ጉልህ የኾነ ችግር እንዳለበት አመላካች ነው። ከወላይታ ድቻ ጋር ያደረጉት ያለግብ አቻ ውጤት በመከላከል ረገድ የተሻለ መሻሻል ያሳዩበት ነበር።

በመቻል በኩል አስቻለው ታመነ እና ግሩም ሀጎስ ከጉዳታቸው ሙሉ ለሙሉ ሲያገግሙ በ5 ቢጫ ካርድ ምክንያት ከጨዋታው ውጭ የነበረው ዳዊት ማሞ ለጨዋታው ዝግጁ ነው ተብሏል። በረከት ደስታ ግን ካጋጠመው ጉዳት ባለማገገሙ ከጨዋታው ውጭ እንደኾነ ተመላክቷል።

የመቀሌ 70 እንደርታ ቡድን በበኩሉ የቅርብ ጊዜ እንቅስቃሴዎቹ ከመቻል በተወሰነ መልኩ የተሻሉ ናቸው። ቡድኑ ከአምስት ጨዋታዎች መካከል አንዱን በድል ሲያጠናቅቅ በአራቱ ላይ ግን ሽንፈትን አስተናግዷል። በተለይም ከአዳማ ከተማ ጋር ያስመዘገቡት የ1ለ0 የድል ውጤት ቡድኑ በተወሰኑ ጊዜያት ተፎካካሪ መኾኑን ያሳየ ኾኖ አልፏል።

ኾኖም ግን ከሌሎች ቡድኖች ጋር ያጋጠሙት ተደጋጋሚ ሽንፈቶች ቡድኑ አሁንም የተረጋጋ አቋም ላይ እንዳልደረሰ ያመለክታሉ። በሁለቱ ቡድኖች ማለትም መቀሌ 70 እንደርታ እና በመቻል መካከል የተደረጉ ጨዋታዎችን ስንመለከት የመቀሌ 70 እንደርታ የተሻለ የበላይነት እንደነበረው መረጃው ያሳያል።

መቀሌ 70 እንደርታ በሦስት ጨዋታዎች አሸንፏል፤ መቻል በበኩሉ አንድ ጨዋታ ብቻ ነው ማሸነፍ የቻለው። እንዲሁም በአንድ ጨዋታ ሁለቱ ቡድኖች ያለ ጎል ተለያይተዋል። በመቐለ 70 እንደርታ በኩል ጉዳት ላይ የነበረው ያሬድ ብርሃኑ ልምምድ ቢጀምርም ለጨዋታ የመድረሱ ነገር አጠራጣሪ ነው፤ ሔኖክ አንጃው እና ተመስገን በጅሮንድ ከጉዳታቸው ባለማገገማቸው በዛሬው ጨዋታ አይሳተፉም።

በአጠቃላይ ሲታይ የመቻል ቡድን በአሁኑ ወቅት የውጤት ማሽቆልቆል እያሳየ ሲኾን መቀሌ 70 እንደርታ በበኩሉ የተሻለ እንቅስቃሴ ለማድረግ እየጣረ ነው የሚገኘው። ጨዋታውም ምሽት 12 ሰዓት ይካሄዳል።

በምሥጋናው ብርሃኔ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here