የፋሲል ከነማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ትኩረት አግኝቷል።

0
102

ባሕር ዳር: መጋቢት 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የደረጃ ሰንጠረዥ ላይ በተከታታይ የተቀመጡት ፋሲል ከነማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ዛሬ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ፋሲል ከነማ በቅርቡ ወልዋሎን በማሸነፍ ወደ ዘጠነኛ ደረጃ ከፍ ማለቱ ይታወሳል።

ቡድኑ በአጠቃላይ 30 ነጥብ በመሠብሠብ ወደፊት እየተጠጋ ነው። አጼዎቹ ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች የማጥቃት አቅማቸው መሻሻሉን አሳይተዋል። በጉዳት ምክንያት በፋሲል ከነማ ሥብሥብ ውስጥ ሀቢብ መሐመድ፣ አፍቅሮተ ሠለሞን እና ተመስገን ካስትሮ እንደማይኖሩ ታውቋል። ቅዱስ ጊዮርጊሶች 31 ነጥብ ይዘው በስምንተኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኙት።

ፈረሰኞቹ ከሁለት ተከታታይ የአቻ ውጤቶች በኋላ ወደ ድል ለመመለስ ነው ጥረት የሚያደረጉት። የፈረሰኞቹ ዋነኛ ችግር የግብ ማስቆጠር ሲኾን ይህም ባለፉት ያደረጋቸው ጨዋታዎች በግልጽ አሳይተዋል። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ሻይዱ ሙስጠፋ፣ ተገኑ ነጋሽ፣ ፍሪምፖንግ ክዋሜ እና አብዱልአዚዝ ቶፊክ ለጨዋታው አይደርሱም።

አጼዎቹ እና ፈረሰኞቹ በፕሪምየር ሊጉ እስካኹን በ16 ጨዋታዎች ተገናኝተዋል። ሁለቱም ቡድኖች እያንዳንዳቸው ሰባት ጊዜ ሲያሸንፉ ሁለት ጨዋታዎችን ደግሞ በአቻ ውጤት ነው የተለያዩት። ጨዋታው ቀን 9:00 ላይ ይካሄዳል። ሌላኛው ጨዋታ በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ የሚገኘው ወልዋሎ አድግራት እና ፕሪምየር ሊጉን በሚመራው ኢትዮጵያ መድን መካከል ይካሄዳል።

ወልዋሎ አድግራት በአስቸጋሪ የውድድር ዓመት ውስጥ የሚገኝ ሲኾን በዘጠኝ ነጥቦች የደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ነው የሚገኘው። በዛሬው ጨዋታም ኡጋንዳዊው አማካይ ሙሳ ራማታህ በቅጣት እንዲኹም በረከት አማረ እና ኤፍሬም ኃይለማርያም በጉዳት ምክንያት እንደማይሰለፉ ታውቋል። ጨዋታውም ቀን 12:00 ላይ የሚጀምር ይኾናል።

ኢትዮጵያ መድን በ44 ነጥቦች የሊጉን ደረጃ እየመራ ይገኛል። ቡድኑ በተከታታይ ሦስት ጨዋታዎችን በማሸነፍ ለዋንጫው የቀረበ ቡድን ለመባል አስችሎታል። የአሠልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ቡድን በጥሩ የተከላካይ መስመር፣ በተጠናከረ አማካይ ክፍል እና የማጥቃት ብቃቱ ከፍተኛ በኾነ የአጥቂ ክፍል ይታወቃል።

በመድን በኩል ሚልዮን ሰለሞን እና ረመዳን የሱፍ በጉዳት ምክንያት ከጨዋታው ውጭ ናቸው። ሁለቱ ቡድኖች በፕሪምየር ሊግ ታሪካቸው ለሁለተኛ ጊዜ የሚገናኙ ሲኾን በመጀመሪያው ዙር ኢትዮጵያ መድን በአብዲሳ ጀማል ብቸኛ ግብ አሸንፏል። የጨዋታው ውጤትም የሁለቱ ቡድኖች የውድድር ዓመት ጉዞ ላይ ወሳኝ ተጽዕኖ ይኖረዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here