ባሕር ዳር: መጋቢት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 23ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ባሕር ዳር ከተማ እና ስሑል ሽረ ይፋለማሉ። ይህ ጨዋታ ለሁለቱም ቡድኖች ወሳኝ ነው። ባሕር ዳር ከተማ ከሊጉ መሪ ያለውን ርቀት ለማጥበብ ሲጥር፣ ስሑል ሽረ ደግሞ ከወራጅ ቡድኖች ዝርዝር ለመውጣት ነው ጨዋታቸውን የሚያደርጉት።
ባሕር ዳር ከተማ በቅርብ ጊዜያት ባሳየው ጥሩ ብቃት ወደ ዋንጫ ተፎካካሪነት ተመልሷል። አኹን ላይ በ33 ነጥቦች ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲኾን ይህንኑ ደረጃውን ለማስጠበቅ ይህንን ጨዋታ ማሸነፍ ይጠበቅበታል። ቡድኑ በመከላከል ረገድ ጠንካራ ቢኾንም፣ የማጥቃት አጨዋወቱን ግን አሻሽሎ ዛሬ መግባት ይኖርበታል። በተለይ ወሳኙ ተከላካይ ፍሬዘር ካሳም ከቅጣት ተመልሶ በሥብሥቡ ውስጥ መኖሩ መልካም የሚባል ነው።
ስሑል ሽረ በ15 ነጥቦች 17ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ከወራጅ ቡድኖች መካከል አንዱ ነው። ይህን ጨዋታ በማሸነፍ ከወራጅ ቡድኖች ዝርዝር ለመውጣት ጠንካራ ፉክክር ያደርጋል ተብሎ ነው የሚጠበቀው። ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ሦስት ጊዜ የተገናኙ ሲኾን ባሕር ዳር ከተማ ሁለት ጊዜ ስሑል ሽረ ደግሞ አንድ ጊዜ ማሸነፍ ችለዋል።
ባሕር ዳር ከተማ በቡድኑ ላይ 4 ግቦችን ሲያስቆጥር፣ ስሑል ሽረ ደግሞ 1 ግብ ብቻ አስቆጥሯል። ጨዋታው ዛሬ ቀን 9 ሰዓት ይካሄዳል። በሌላ 23ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ መርሐ ግብር መቻል እና ኢትዮጵያ ቡናን በሊጉ አገናኝቷል። ይህ ጨዋታ በብዙዎች ዘንድ ተጠባቂ ነው። በተለይ ደግሞ መቻል ከአዳማ ከተማ ጋር ባደረጋቸው ጨዋታዎች ደካማ ውጤት በማስመዝገቡ በደረጃ ሰንጠረዡ ላይ ከፍተኛ መውረድ አሳይቷል።
በመኾኑም ይህን ጨዋታ በማሸነፍ ወደ ቀድሞ ቦታቸው ለመመለስ ከፍተኛ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎም ነው የሚጠበቀው። በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ቡና በሊጉ ጥሩ የሚባል ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው። ባለፉት አምስት ጨዋታዎችም ላይ መረባቸውን አላስደፈሩም። ይኹን እንጅ የግብ ማስቆጠር ችግር አኹንም ይታያል።
በሁለቱ ክለቦች መካከል በተደረጉ 35 ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ቡና 18 ጊዜ ሲያሸንፍ መቻል ሰባት ጊዜ አሸንፏል። ዛሬ ምሽት 12 ሰዓት የሚካሄደው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ከፍተኛ ፉክክር እንደሚታይበት ይጠበቃል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን