“ልዩው ሰው” በአወዛጋቢነታቸው ቀጥለዋል።

0
135

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ‎ራሳቸውን “ልዩው ሰው” ብለው ለዓለም ያስተዋወቁት አነጋጋሪው አሠልጣኝ ጆሴ ሞሪንሆ የአሠልጣኝነት ስኬታቸው በብዙዎች የሚቀናበት ነው። ሰውየው በ2004 ፖርቶን እየመሩ የአውሮፖ ሻምፒዮንስ ሊግን በማሸነፍ ነው ራሳቸውን ለገብያ ያቀረቡት።

ወዲያው የቼልሲ የለውጥ አብዮትን የተተቀላቀሉት ጆዜ በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ከወቅቱ ኅያላን የፈርጉሰኑ ማንቸስተር ዩናይትድ እና ከቬንገሩ አርሰናል በላይ ለመኾን ጊዜ አልወሰዱም። በወጡበት ዓመት ቼልሲን የፕሪምየር ሊግ አሸናፊ አደረጉት። በቼልሲ በሁለት በተከፈለ ቆይታቸው ፕሪምየር ሊጉን ጨምሮ ሌሎች የውስጥ ውድድሮች ላይ በተደጋጋሚ ክለቡን አንግሰውታል።

ፖርቱጋላዊ አሠልጣኝ በጣሊያኑ ኢንተር ሚላን የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግን ጨምሮ ሌሎች ዋንጫዎችንም አሳክተዋል። ወደስፔን ተጉዘውም በኅያሉ ሪያልማድሪድ የራሳቸውን አሻራ አስቀምጠዋል። ወደ እንግሊዝ ተመልሰው ማንቸስተር ዩናይትድን፣ በጣሊያንም ሮማን አሠልጥነዋል። ሰውየው ካሠለጠኗቸው ክለቦች ከቶትንሃም ውጭ ዋንጫዎችን ማንሳት የቻሉ የውጤት ተምሳሌት ናቸው።

ከእነዚህ ሁሉ ስኬቶቻቸው በላይ ግን ጆዜ አወዛጋቢ ድርጊቶቻቸው እና ንግግራቸው ይቀድማል። በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የፈርጉሰን እና ቪንገርን የሚዲያ ተፈላጊነት የቀለበሱት ሞሪንሆ በተለይ ከቪንገር ጋር አንገት ለአንገት እስከ መተናነቅ ደርሰዋል። በተለያዩ ጊዜያት በቃላት ፈረንሳዊውን በመተቸትም ይታወቃሉ።

በስፔን ቆይታቸውም ከአሠልጣኝ እስከ ተጫዋች ያልተነኮሱት የለም። የባርሴሎና አሠልጣኝ የነበሩት የቲቶ ቮላኖቫን ጆሮ ከመቆንጠጥ እስከ ተጋጣሚ ተጫዋች ላይ ታዝሎ መጨፈር “ልዩው ሰው” ያላደረጉት ልዩ ነገር የለም። ሞሪንሆ ቤቴ ለሚሉት ቼልሲም የሚመለሱ ሰው አይደሉም። የማንቸስተር ዩናይትድ አሠልጣኝ ኾነው ቼልሲን በገጠሙባቸው ጨዋታዎች የቼልሲ ምክትል አሠልጣኝን እገላለሁ ብለው ከመገልገል እስከ ቼልሲ ደጋፊዎች ክብር ስጡኝ ጥያቄ መነጋገሪያ ድርጊቶችን ፈጽመዋል።

ሰውየው አኹን በቱርክየ ይገኛሉ። ፌነርባቼን እየመሩም ነው። አነጋጋሪው አሠልጣኝ በቱርክየም የሚዲያ ሙቀት ኾነው ቀጥለዋል። ሞሪንሆ ቱርክየን እግራቸው እንደረገጠ “ይሄ መለያ ደሜ ነው” ብለው ለሚዲያዎች ርዕስ ሰጡ። ከሳምንታት በፊት በተቀናቃኞቹ ጋላታሳራይ እና ፌነርባቼ ጨዋታ ሞሪንሆ በጋላታሳራይ ጥቁር ተጫዋቾች ላይ የዘረኝነት ስድብ ሰንዝረዋል ተብለው ተከሰው ነበር። ጥፋተኛ ተብለውም ቅጣት ተጥሎባቸዋልም።

እሳቸው ግን ከአፍሪካውያን ተጫዋቾች ጋር ያለኝን መልካም ግንኙነት ለማጉደፍ የተደረገ ሴራ ነው ብለው አቃለውታል። አንደ ፈርስት ስፖርት መረጃም እነዲዴ ድሮግባን የመሳሰሉ የድሮ ኮከቦቻቸውም ሞሪንሆ መቼም ቢኾን ዘረኛ ሊኾኑ አይችሉም ብለው ሞግተውላቸዋል። አወዛጋቢነትን መለያ ያደረጉት ሞሪንሆ አኹንም በአዲስ ክስተት ዓለምን እያነጋገሩ ነው። ትናንት ምሽት ቡድናቸው ፌነርባቼ ከጋላታሳራይ ጋር ተጫውቷል።

በጨዋታው ቡድናቸው 2ለ1 የተሸነፈባቸው ጆዜ የጋላታሳራዩን አሠልጣኝ ኦካር ብሩክስን አፍንጫ ጎትተው ሜዳ ላይ በመዘረር ሜዳውን ወደ ጸብ ቀይረውታል። ጆዜ ለድርጊታቸው ቅጣት ሊጠብቃቸው እንደሚችልም ይጠበቃል። በጨዋታው ከሁለቱም ቡድኖች ሦስት ተጫዋቾች በቀይ ካርድ ወጥተዋል።

በአስማማው አማረ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here