ባሕር ዳር፡ መጋቢት 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በመርሲሳይድ ደርቢ የሊቨርፑል ከኤቨርተን የሚገናኙበት ዛሬ ተጠባቂ ነው። ጨዋታው ምሽት 4:00 በአንፊልድ ይካሄዳል። በዚህ ጨዋታ የሊቨርፑል የቀኝ ተከላካይ ኮኖር ብራድሌይ ከጉዳቱ አገግሞ ወደ ሜዳ ሊመለስ ይችላል ተብሏል። ራያን ግራቨንበርች እና ግብ ጠባቂው አሊሰን ቤከርም ለጨዋታው ዝግጁ መኾናቸው ተረጋግጧል።
በኤቨርተን በኩል ደግሞ ኢሊማን ንዲዬ እና ድዋይት ማክኒል ሙሉ ልምምድ መጀመራቸው ተገልጿል። ነገር ግን በጨዋታው ስለመሰለፋቸው እርግጠኛ መኾን አልተቻለም። ቪታሊይ ሚኮለንኮ ከጉዳቱ አገግሞ ወደ ሜዳ እንደሚመለስም ተገልጿል።
ሊቨርፑል ባለፉት ሦስት የመርሲሳይድ ደርቢ ጨዋታዎች በአንፊልድ ድል ቀንቶታል። ኤቨርተን ከ1999 ወዲህ በአንፊልድ ያሸነፈው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። በሁለቱ ቡድኖች መካከል በተደረጉ ጨዋታዎች 25 ቀይ ካርዶች ተመዝግበዋል፣ ይህም በፕሪምየር ሊጉ ከፍተኛው ነው።
ሊቨርፑል በ25 የሊግ ጨዋታዎች ያልተሸነፈ ሲኾን ይህም በታሪኩ ሦስተኛው ነው። ኤቨርተን በዘንድሮው የውድድር ዘመን 13 ጊዜ አቻ ወጥቷል፤ ይህም ከሌሎች ቡድኖች የበለጠ ነው። ዴቪድ ሞይስ ከሊቨርፑል ጋር ባደረጓቸው 19 የፕሪምየር ሊግ የሜዳ ውጭ ጨዋታዎች አላሸነፉም።
በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ምሽት ሌላ ጨዋታ ማንቸስተር ሲቲ ከሌስተር ሲቲ ይጫወታሉ። በዚህ ጨዋታ የማንቸስተር ሲቲ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ኤርሊንግ ሃላንድ በቁርጭምጭሚት ጉዳት እንደማይሰለፍ ተረጋግጧል። እስከ ሰባት ሳምንታት ከሜዳ እንደሚርቅ ተነግሯል።
በተጨማሪም ሮድሪ፣ ናታን አኬ፣ ማኑኤል አካንጂ እና ጆን ስቶንስ በጉዳት ምክንያት ከቡድኑ ሥብሥብ ውጭ ናቸው። በሌላ በኩል የሌስተር ሲቲው ሪካርዶ ፔሬራ ከጉዳት ሊመለስ እንደሚችል ሲጠበቅ የክንፍ አጥቂው አብዱል ፋታው በጉልበት ጉዳት ምክንያት ከቡድኑ ውጭ ስለመኾኑ ነው የተነገረው።
ማንቸስተር ሲቲ በቅርብ ጊዜ በተደረጉት ስድስት የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ሦስት ሽንፈቶችን አስተናግዷል፣ እነዚህ ሽንፈቶች የመጡት ከሊቨርፑል፣ አርሰናል እና ኖቲንግሃም ፎረስት ጋር ሲጫወት ነው። ሌስተር ሲቲ በአስቸጋሪ ጊዜ ውስጥ እያለፈ ነው። ቡድኑ ባለፉት 14 የሊግ ጨዋታዎች 13 ሽንፈቶችን አስተናግዷል፣ በአጠቃላይ አራት ግቦችን ብቻ አስቆጥሯል።
ከሜዳው ውጭ በዚህ የውድድር ዘመን 35 ጎሎች ተቆጥረውበታል። ሌስተር ሲቲ በዚህ የውድድር ዘመን በ29 የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ውስጥ 24 ጊዜ ጎል ተቆጥሮበታል፣ ይህም ከሌሎች ቡድኖች የበለጠ ነው።
በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ምሽት ሌሎች ጨዋታዎቾም ሲካሄዱ በርንዝ ማውዝ ከኢፒሲችታውን፣ ብራይተን ከአስቶንቪላ፣ ኒውካስትል ከብሬንትፎርድ፣ ሳውዛምፕተን ከክርስታል ፓላስ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በምሥጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!