9ኛው የመላው አዊ ብሔረሰብ ስፓርታዊ ጨዋታዎች ውድድር በእንጅባራ ከተማ መካሄድ ጀመረ።

0
108

እንጅባራ: መጋቢት 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 9ኛው የመላው አዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ስፓርታዊ ጨዋታዎች ውድድር “ስፖርት ለሰላም፣ ሰላም ለሁሉም ” በሚል መልዕክት በእንጅባራ ከተማ መካሄድ ጀምሯል። ውድድሩ በ5 የስፖርት አይነቶች እንደሚካሄድ ተመላክቷል።

በውድድሩ መክፈቻ መርሐ ግብር ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የእንጅባራ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ የኔዓለም ዋሴ ውድድሩ ከውጤት ባሻገር በወረዳዎች እና በከተሞች መካካል ልምድ ለመለዋወጥ እና ማኅበራዊ ትስስርን ለማጠናከር የሚያግዝ መኾኑን ተናግረዋል።

ስፖርተኞች በቆይታቸው ስፖርታዊ ጨዋነትን በመላበስ ውድድሮችን እንዲያካሂዱም ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አስገንዝበዋል። ከተማ አሥተዳደሩ የመላው አዊ ብሔረሰብ ስፖርታዊ ውድድርን ለማስተናገድ የሚያስችል በቂ ዝግጅት አድርጓልም ነው ያሉት።

የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ቃለአብ ከሃሊ ውድድሩ በጸጥታ ችግር ምክንያት ተቀዛቅዞ የቆየውን ስፖርታዊ እንቅስቃሴ የሚያነቃቃ መኾኑን ተናግረዋል። ከመጋቢት 23 እስከ 28/2017 ዓ.ም ድረስ ለ6 ተከታታይ ቀናት በሚካሄደው በዚህ ውድድር ከብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከ10 ወረዳዎች እና ከተማ አሥተዳደሮች የተውጣጡ ከ700 በላይ ስፖተኞች ይሳተፉበታል ነው ያሉት።

በውድድሩ የተሻለ ውጤት የሚያስመዘግቡ ስፖርተኞች በቀጣይ በደሴ ከተማ በሚካሄደው 9ኛው የመላው አማራ ስፖርታዊ ውድድሮች ብሔረሰብ አሥተዳደሩን ወክለው የሚሳተፉ ይሆናልም ተብሏል። የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክትል አሥተዳዳሪ እና የከተማና መሠረተ ልማት መምሪያ ኀላፊ አይተነው ታዴ ተተኪ ስፖርተኞችን የማፍራት ሂደት የሁሉንም ተሳትፎ እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።

በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ስፖርታዊ ውድድሮች በመቀዛቀዛቸው ተተኪ ስፖርተኞችን የማፍራቱ ሂደት ፈተና ገጥሞት መቆየቱን ተናግረዋል። በአካሉና በአእምሮው የዳበረ ትውልድ ለመገንባት የሁሉንም ርብርብ እንደሚጠይቅም አስገንዝበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here