“ለእግር ኳሳችን ዘላቂው መፍትሄ ታዳጊዎች ላይ መሥራት ነው” የቀድሞው የብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ሚካኤል ጆርጅ

0
224

ደሴ፡ መጋቢት 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በብሔራዊ ቡድን ተጫዋችነት እንዲሁም በተለያዩ የፕሪሚየርሊግ ክለቦች ተጫውቶ ያሳለፈው ሚካኤል ጆርጅ (ሚኪ ጆርጅ) በእሱ ዘመንም ኾነ አሁንም ባሉት የታዳጊዎች ፈተና የትጥቅ ችግር እንደኾነ አንስቷል።

የእግር ኳሳችን ትልቁ ድክመት ተተኪ ታዳጊዎችን ማፍራት አለመቻል መኾኑን የሚገልጸው ሚካኤል ጆርጅ (ሚኪ ጆርጅ) በስፓርቱ ያለፉ ሁሉ የነገ ተስፋዎች ላይ መሥራት አለባቸው ብለዋል። ይህ ሲኾን የእግር ኳሱ ትንሳዔ እሩቅ እንደማይኾንም አመላክቷል።

እግር ኳስን በፕሮጀክት ታቅፎ በጀመረባት ደሴ ከተማ በመገኘት በአምስት ፕሮጀክቶች ለታቀፉ 150 ወጣቶች 250 ሺህ ብር ወጭ በማድረግ የትጥቅ ድጋፍ አድርጓል።

ድጋፏን ባስረከበበት ወቅት እንደተናገረው በሕጻናት እና ታዳጊዎች ላይ ለስፖርቱ የሚያገለግሉ አልባሳት አለመሟላት ስፓርተኞችን እና አሠልጣኞችን ተስፋ የሚያስቆርጥበት ሁኔታ በመኖሩ ይህን ለማቃለል የተደረገ ድጋፍ መኾኑን ተናግሯል።

አሁን ላይ ደሴ ከነማ የእግር ኳስ ክለብ ወደ ተሻለ ደረጃ እየሄደ ስለኾነ አጋዥ የኾኑ ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ እንዲሁም ለማደራጀት እንዲቻል በከተማዋ እና በውጭ የሚገኙ ጓደኞቹን በማስተባበር ብሎም የራሱን አስተዋጽኦ በማረግ በተሠበሠበው ገንዘብ በአምስት ፕሮጀክቶች ውስጥ ለታቀፋ ለ150 ወጣት እና ታዳጊዎች 250 ሺህ ብር ወጭ በማድረግ የማልያ ድጋፍ መደረጉንም ጠቁሟል።

300 የኳስ መጫወቻ ጫማ እና ሌሎች ቁሳቁሶችን በመጨመር በቀጣይም ወጣት እና ታዳጊዎቹ የተሻለ ደረጃ እንዲደርሱ በሰፊው ድጋፉን እንቀጥላለን ነው ያለው።

ሚካኤል ጆርጅ “ለእግር ኳሳችን ዘላቂው መፍትሄ ታዳጊዎች ላይ በርብርብ መሥራት ነው” ብሏል።

ድጋፍ የተደረገላቸው ታዳጊዎች እና አሠልጣኞች ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት በስፓርቱ ውስጥ ተፈትነው ያለፉ እና ስኬታማ የነበሩ ተጫዋቾች በዘርፉ ያለውን ፈተና ስለሚረዱት ድጋፉን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

ሚካኤል ጆርጅ (ሚኪ ጆርጅ) ጓደኞቹን በማስተባበር እና የራሱን አበርክቶ በመጨመር ስላደረገው ነገር ሁሉ አመሥግነዋል።

የደሴ ከተማ ወጣት እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ሰይድ አራጋው ስፖርት በመንግሥት ብቻ የሚደገፍ ባለመኾኑ የከተማዋ ተወላጆች፣ ባለሃብቶች እና የቀድሞ ተጫዋቾች የሚያደርጉት ድጋፍ አበረታች መኾኑን ገልጸው አመሥግነዋል።

ሚካኤል ጆርጅ ለታዳጊዎች እና ለወጣቶች ተሞክሮን ማካፈሉ እና ድጋፍ ማድረጉ ታዳጊዎችን የተሻለ ደረጃ እንዲደርሱ መነሳሳትን የሚፈጥር ነው ብለዋል።

ዘጋቢ:- ተመስገን አሰፋ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here