ባሕር ዳር፡ መጋቢት 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች መካከል የዝውውር ወሬዎች እየወጡ ነው፡፡ ስድስት የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የሊልን ካናዳዊ አጥቂ ጆናታን ዴቪድን ለማስፈረም ፍላጎት አሳይተዋል፡፡ ኒውካስል፣ ማንቸስተር ዩናይትድ፣ ቶተንሃም፣ ዌስትሃም፣ ቼልሲ እና ሊቨርፑል ፈላጊዎቹ ናቸው፡፡
ማንቸስተር ዩናይትድ የኤቨርተንን እና የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ተከላካይ ጃራድ ብራንትዌትን ለማስፈረም ፍላጎት አሳይቷል፡፡ ሊቨርፑል በፍራንክፈርት የሚጫወተውን የ22 ዓመቱን ፈረንሳዊ አጥቂ ሁጎ ኤኪቲኬን ለማስፈረም ከአርሰናል ጋር እየተፎካከሩ ነው፡፡
ማንቸስተር ዩናይትድ ኤኪቲኬን ለማስፈረም ከኒውካስል እና ከሌሎች የአውሮፓ ክለቦች ጋር ፉክክር ገጥሟል፡፡ ኖቲንግሃም ፎረስት፣ አርሰናል እና ሊቨርፑል የኡዲኔዜን እና የጣሊያንን አጥቂ ሎሬንዞ ሉካን ለማስፈረም ፍላጎት ሲያሳዩ ማንቸስተር ዩናይትድ እና ዌስትሃም ፈረንሳዊ ተከላካይ ኦማር ሶሌትን ለማስፈረም እየተከታተሉት ይገኛሉ፡፡
ሊቨርፑል የእንግሊዙን ተከላካይ ጃሬል ኳንሳ ለቀጣዩ የውድድር ዘመን እያዘጋጀ ሲኾን ኒውካስል ፍላጎት ቢያሳይም ሊቨርፑል ተጫዋቹን ለመሸጥ ዕቅድ እንደሌለው ነው ቢቢሲ ያስነበበው፡፡
የቀድሞው የማንቸስተር ዩናይትድ አሠልጣኝ ኦሌ ጉነር ሶልሻየር የሚያሰለጥኑት ቤሺክታሽ የኢፕስዊች ታውንን የክንፍ ተጫዋች ጃደን ፊሎገንን በውሰት ለማስፈረም ፍላጎት አሳይተዋል፡፡ ማንቸስተር ሲቲ እና ሊቨርፑል የባየር ሌቨርኩሰንን የቀኝ ተከላካይ ጄረሚ ፍሪምፖንግን ለማስፈረም እየተሽቀዳደሙም ይገኛሉ፡፡
ኖቲንግሃም ፎረስት ከኤሲ ሚላን በውሰት ሮማ ውስጥ የሚጫወተውን ቤልጅየማዊ የክንፍ ተጫዋች አሌክሲስ ሳሌማከርስን ለማስፈረም ፍላጎት አሳይቷል፡፡
ኤቨርተን የሰንደርላንድን እንግሊዛዊ አጥቂ ክሪስ ሪግ እና አማካዩን ዳን ኔልን ለማስፈረም ፍላጎት አሳይቷል፡፡
ቶተንሃም የቀድሞውን አሠልጣኝ ፋቢዮ ፓራቲቺን ወደ ክለቡ ለመመለስ ፍላጎት ሲያሳይ ኤሲ ሚላንም ጣሊያናዊውን አሠልጣኝ ይፈልገዋል ነው የተባለው፡፡
ባየር ሙኒክ በክለቦች የዓለም ዋንጫ ላይ እንዲጫወቱ ቶተንሃምን ጨምሮ ከሌሎች ክለቦች የወሰዳቸውን ተጫዋቾች ከውሰት ጊዜው ቀድሞ ሊመልስ እንደሚችል ነው እየተዘገበ ያለው፡፡ ይህም የ19 ዓመቱን ፈረንሳዊ አጥቂ ማቲስ ቴልን እንደሚጨምር ቢቢሲ በጭምጭምታ አምዱ አስፍሯል፡፡
በምሥጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!