በስፋት እየተዘዋወሩ ያሉ የዝውውር ወሬዎች፦

0
170

ባሕር ዳር: መጋቢት 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ክለቦች በቀጣይ ዓመት የተሻለ ጠንክረው ለመቅረብ ከወዲሁ የሚፈልጓቸውን ተጫዋቾች እየመለመሉ ነው። እንደ ቢቢሲ ዘገባም በርካታ ተጫዋቾች እና አሠልጣኞች ከተለያዩ ክለቦች ጋር ስማቸው እየተያያዘ ነው።

ረያል ማድሪድ እንግሊዛዊን የቀኝ ተከላካይ አሌክሳንደር አርኖልድ ለማስፈረም መስማማቱ ማርካን ጨምሮ በርካታ የስፖርት ምንጮች ጽፈዋል። ተጫዋቹ የሊቨርፑል ዉሉ የሚጠናቀቀው ሰኔ ላይ በመኾኑ በነጻ ዝውውር ነው በርናቦ የሚደርሰው።

ተጨማሪ ወሳኝ ተጫዋቾቹን በነጻ የማጣት ስጋት ያለበት ሊቨርፑል መሀመድ ሳላህን እና ቨርጂል ቫንዳይክን ለማቆየት ፈተና ወስጥ ይገኛል። አትሌቲኮ ማድሪድ የቶተንሃሙን አርጀንቲናዊ የመሐል ተከላካይ ክርስቲያን ሮሜሮን ለማስፈረም ፍላጎት አሳይቷል።

አርጀንቲናዊ ተከላካይ በቶትንሃም እና አርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው። ኤቨርተን በማንቸስተር ዩናይትድ የሚፈለገውን ጃራድ ብራንትዋይትን ለማቆየት አዲስ ውል አቅርቧል። ማንቸስተር ዩናይትድ የ32 ዓመቱን እንግሊዛዊ የመሐል ተከላካይ ሃሪ ማጉዌር ኦልድትራፎርድን ከለቀቀ ብቻ ብራንዝዋይትን ለማስፈረም ጥረት እንደሚያደርግም ተገልጿል።

የአርሰናሉ ብራዚላዊውን የመሐል ተከላካይ ጋብርኤልን ማጋሊሽ በሳውዲ አረቢያ ክለቦች አይን ውስጥ ገብቷል። አርሰናል ይሄን የሳውዲ ክለቦች ፍላጎት ለማርገብ ለጋብሬል አዲስ ውል ለማቅረብ ወስኗል። ሌላኛው የመድፈኞቹ የመሀል ተከላካይ ዊሊያም ሳሊባ ደግሞ በሪያል ማድሪድ እየተፈለገ ነው። የስፔኑ ክለብ በየጊዜው ጉዳት የሚፈትናቸውን የመሀል ተከላካዮችን የሚተካለት ሁነኛ ተጫዋች ሳሊባ ነው በሚል በተደጋጋሚ ይነሳል።

አታላንታ በማንቸስተር ዩናይትድ እና በኒውካስትል ዩናይትድ የሚፈለገውን አዴሞላ ሉክማንን በ50 ሚሊዮን ፓውንድ ለመሸጥ ወስኗል። አስቶንቪላ ፈረንሳዊ አማካይ ቡባካር ካማራን አዲስ ውል ለማስፈረም ንግግር መጀመሩ ታውቋል።

ክሪስታል ፓላስ ለአሠልጣኙ ኦሊቨር ግላስነር ተጨማሪ ውል የማቅረብ ፍላጎት አለው። ምክኒያቱ ደግሞ አሠልጣኙ በጀርመኑ አርቢ ሊፕዚግ እየተፈለጉ በመኾኑ ነው በማለት ቢቢሲ በስፖርት አምዱ አስነብቧል።

በምሥጋናው ብርሃኔ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here