ባሕር ዳር: ጥር 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በ34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በዛሬው መርሐ ግብሩ አልጀሪያ ከቡርኪና ፋሶ፤ ሞሪታኒያ ከአንጎላ፤ ቱኒዚያ ከማሊ ወሳኝ ጨዋታዎችን ያደርጋሉ፡፡
በምድብ አራት የሚገኙት አልጄሪያ እና ቡርኪና ፋሶ ቀን 11 ሰዓት ላይ 40 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው ዴ ላ ፓክስ ስታዲየም ይጫወታሉ፡፡
ሁለቱ ሀገራት በአፍሪካ ዋንጫ ሲገናኙ የአሁኑ ለሶስተኛ ጊዜ መኾኑ ነው፡፡ ቡድኖቹ እስካሁን በሁሉም ውድድሮች 18 ጊዜ ተገናኝተዋል። ተቀራራቢ ፉክክርም አድርገዋል፡፡
አልጄሪያ የአፍሪካ ዋንጫን ሁለት ጊዜ በመውሰድ ከቡርኪና ፋሶ ከፍ ያለ ታሪክ አላት፡፡
አልጄሪያ እስከ መጋቢት ወር 2023 ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ባደረገቻቸው 12 ጨዋታዎች በአንድም ጨዋታ አልተሸነፈችም። በ34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በመጀመሪያው የምድብ ጨዋታ ከአንጎላ ጋር አንድ አቻ በመለያየቷ ያላት ነጥብ አንድ ብቻ ነው፡፡ ስለኾነም የዛሬውን ጨዋታውን በአሸናፊነት ለመወጣት ብርቱ ፉክክር ታደርጋለች ተብሎ ይጠበቃል፡፡
እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1996 ደቡብ አፍሪካ ባዘጋጀችው 20ኛው የአፍሪካ ዋንጫ አልጄሪያ ቡርኪና ፋሶን 2 ለ 1 ማሸነፏን ቢቢሲ አስታውሷል፡፡
አልጀሪያውያኑ የበረሀ ቀበሮዎቹ ከአፍሪካ ሀገራት በእግር ኳስ በሶስተኛ ደረጃ ላይም ይገኛሉ፡፡
ስታሊኖች (ቡርኪና ፋሶ) በ34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ሞሪታንያን በማሸነፍ በሶስት ነጥብ ምድቡን ይመራሉ። ነገርግን በዛሬው ቡርኪና ፋሶ አቻ ብትወጣ እና አንጎላ ሞሪታኒያን ከረታች ሁለቱ ቡድኖች በነጥብ እኩል ይኾኑና በግብ ክፍያ ብቻ ደረጃቸው የሚወሰን ይኾናል፡፡ስለኾነም ስታሊኖች ካሸነፉ በቀጥታ ስለሚያሳልፋቸው ጨዋታውን በትኩረት ያደረጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በዚሁ ምድብ አራት ሞሪታኒያ ከአንጎላን ምሽቱ 2 ሰዓት ላይ በዴ ላ ፓክስ ስታዲየም ያገናኛሉ።
ሁለቱ ሀገራት ከዚህ ቀደም በአፍሪካ ዋንጫ አንድ ጊዜ ተገናኝተዋል፡፡ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2019 ግብጽ ባዘጋጀችው 32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ባደረጉት ጨዋታም ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል።
ሞሪታኒያ ባለፉት ስድስት የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎች ግብ ማስመዝገብ አለመቻሏ የቡድኗን ደካማነት ያሳያል ተብሏል፡፡
ሞሪታኒያ በ34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በመጀመሪያ ጨዋታዋ በቡርኪና ፋሶ 1 ለ 0 ተሸንፋለች፡፡ ስለኾነም በምድቧ ያላትን ተስፋ ለማለምለም የግድ የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍ ይኖርባታል፡፡
አንጎላም በመክፈቻው ጨዋታ ከአልጄሪያ ጋር አንድ አቻ በመውጣቷ ያላት ነጥብ አንድ ብቻ በመኾኑ አሸንፋ ነጥቧን አራት ለማድረስ ብርቱ ትግል ይጠብቃታል ሲል ዴይሊ ሜይል ስፖርት አስነብቧል፡፡
የእግር ኳስ ጨዋታዎችን ቅድመ ውጤት የሚተነብየው ኦፕታ ሱፐር ኮምፒዩተር በጨዋታው አንጎላ ሞሪታኒያን ታሸንፋለች ሲል ግምቱን አስፍሯል፡፡
ምሽቱ 5 ሰዓት ምድብ አምስት ላይ የሚገኙት ቱኒዚያ ከማሊ 20 ሺህ ተመልካች በሚይዘው አማዱ ጎን ኩሊባሊ ስታዲየም ይጫወታሉ፡፡
ሁለቱ ሀገራት ከዚህ ቀደም በአፍሪካ ዋንጫ ሶስት ጊዜ ተገናኝተው ማሊ ሁለት ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዛለች፡፡አንድ ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
የአንድ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዋ ቱኒዚያ በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታዋ በናምቢያ 1 ለ 0 ተሸንፋለች። በአንጻሩ ማሊ ደቡብ አፍሪካን 2 ለ 0 በመርታት ባለ ሶስት ነጥብ ዲታ ናት፡፡
የኾነ ሆኖ ማሊ የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈች ወደ ጥሎ ማለፉ መግባቷን ታረጋግጣለች። ቱኒዚያ ካሸነፈች ግን ነጥቧን አራት በማድረስ ሌሎች ጨዋታዎች አጓጊ ኾነው ይጠበቃሉ፡፡
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!