የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዛሬ ተጠባቂ ጨዋታን ያደርጋል።

0
181

ባህር ዳር: መጋቢት 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ2026 የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከግብጽ አቻው ጋር ይጫወታል። በሀገሩ ደረጃውን የጠበቀ ስታድየም የሌለው ስደተኛው ብሔራዊ ቡድን ወደ ሞሮኮ ተጉዞ ነው ከግብጽ ብሔራዊ ቡድን ጋር የሚጫወተው።

በአፍሪካ ሀገራት የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከግብጽ፣ ከሴራሊዮን፣ ከጊኒ ቢሳው፣ ከቡርኪናፋሶ እና ከጅቡቲ ጋር በምድብ ሀ የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እስካኹን ካደረጋቸው አራት ጨዋታዎች አንዱንም ማሸነፍ አልቻለም። በሦስቱ አቻ ሲለያይ በአንደኛው ጨዋታ ደግሞ ተሸንፏል።

ከአራት ጨዋታዎች ሦስት ነጥቦችን ብቻ ማሳካት የቻለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጅቡቲን ብቻ ቀድሞ አምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ብሔራዊ ቡድኑ ሦስት የግብ ዕዳዎችም አሉበት። የዛሬ ተጋጣሚው የግብጽ ብሔራዊ ቡድን የምድቡ መሪ ነው። ካደረጋቸው አራት ጨዋታዎች ሦስቱን አሸንፎ በአንደኛው ደግሞ አቻ ተለያይቷል። አስር ነጥብ በመያዝም ምድቡን እየመራ ነው።

ሞሐመድ ሳላህ እና ኦማር ማርሙሽን የመሳሰሉ ከዋክብትን የያዘው የግብጽ ብሔራዊ ቡድን ዛሬም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ፈተና እንደሚኾን ይጠበቃል። በሀገሩ ሜዳ እና በደጋፊው ፊት የመጫወት ዕድልን ያጣው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ይሄም ለውጤት ማጣቱ እንደ አንድ ምክንያት ይቆጠራል።

የኢትዮጵያ እና የግብጽ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ አምስተኛ የምድብ ጨዋታ ዛሬ ሞሮኮ ካዛብላንካ በሚገኘው ላርቢ ዛውሊ ስታዲዬም ምሽት 6:00 እንደሚካሄድ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል። በአሠልጣኝ መሳይ ተፈሪ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ግብጽን አሸንፎ ነጥቡን ያሳድግ ይኾን? የሚለው በጉጉት የሚጠበቅ ነው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here