ባሕር ዳር: መጋቢት 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሰባት ተፎካካሪዎች ብርቱ ዘመቻ ያደረጉበት የአለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንትነት ተከናውኗል። የ41 ዓመቷ ክርስቲ ኮቨንትሪም ሳይጠበቁ ማሸነፍ ችለዋል። የዝባብዌ ዜጋዋ ኮቨንትሪ በኦሎምፒክ በውሃ ዋና ውድድር የሁለት ወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ናቸው።
ከምርጫው አስቀድሞ የአለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር የወቅቱ ፕሬዚዳንት ሰባስቲያን ኮ እንደሚያሸንፉ ግምት አግኝተው ነበር።
የሰባስቲያን ኮ አለመመረጥ እንደ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ እና ኔዘርላንድ ለመሳሰሉት ሀገራት እንደ መልካም ተቆጥሯል። ምክንያቱ ደግሞ የቀድሞ 1500 ሜትር ተወዳዳሪ የነበሩት ሰባስቲያን ኮ ኢትዮጵያን ጨምሮ የተጠቀሱት ሀገራት ውጤታማ የኾኑባቸውን የረጅም ርቀት ውድድሮች ከውድድር ዘርፍ ለማስወጣት እቅድ እንደነበራቸው ደጋግመው በመናገራቸው ነው።
አዲሷ የአለም አቀፍ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ተመራጭ ክርስቲ ኮቨንትሪ “አለም የሚወደውን የአትሌቲክስ ስፖርት እንዲያድግ እና በኦሎምፒክ በእኩልነት እና ፍትሐዊነት እንዲተገበር እሠራለሁ” በማለት ቃል ገብተዋል። የክርስቲና ኮቬንትሪ ማሸነፍ የአፍሪካውያን ተጽዕኖ ፈጣሪነት እያደገ ስለመምጣቱ ማሳያ ተደርጓል።
ኮቨንትሪ በታሪክ የኦሎምፒክ ኮሚቴን በፕሬዝዳንትነት በመመራት የመጀመሪያ ሴት መኾናቸውን ቢቢሲ በስፖርት ገጹ አስነብቧል። ግለሰቧ የዝባብዌ የስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ናቸው።
በመልሰው ጥበቡ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!