ደሴ ከተማ እሁድ ወሳኝ ጨዋታውን ከነገሌ አርሲ ከተማ ጋር ያደርጋል።

0
169

ባሕር ዳር: መጋቢት 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ “ለ“ የተደለደለው የደሴ ከተማ እግር ኳስ ቡድን እስካሁን 16 ጨዋታዎችን አድርጓል፡፡ ዘጠኝ ጨዋታዎችንም አሸንፏል፡፡ በአምስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል፡፡ ቡድኑ ካደረጋቸው 16 ጨዋታዎች የተሸነፈው በሁለት ጨዋታዎች ብቻ መኾኑ የቡድኑን ጥንካሬ ያመላክታል፡፡

32 ነጥብ ሠብሥቦ ከምድቡ መሪ ነገሌ አርሲ ከተማ በአንድ ነጥብ ተበልጦ እና 19 ንጹህ ግብ በመሠብሠብ በሁለተኛነት ተቀምጧል፡፡ ቡድኑ የፊታችን እሑድ ከነገሌ አርሲ ከተማ ጋር ቀን 10:00 ሰዓት ወሳኝ ጨዋታ ያደርጋል፡፡ ነገሌ አርሲ ከተማ ደሴ ከተማን በአንድ ነጥብ በልጦ ቢመራውም ደሴ ከተማ በበኩሉ ተጋጣሚውን በአራት ንጹህ የግብ ክፍያ ይበልጠዋል፡፡ ይህም ለቡድኑ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡

ደሴ ከተማዎች ኳስን አረጋግተው ይጫወታሉ፡፡ ከጨዋታ ጨዋታም የአጨዋወት ብስለትን አዳብረዋል፡፡ ማሳያው ደግሞ ኳስን መስርተው መጫወታቸው እና የተጫዋቾች ትኩረት ላቅ እያለ መምጣቱ ነው፡፡ ያሟሟቁትን ጨዋታ ሳያቀዘቅዙ በመቀጠልም ይታወቃሉ፡፡ በ16ኛው ሳምንት ሱሉልታ ክፍለ ከተማን 2 ለ 0 ሲረቱ ግቦቹን ያስቆጠሩት በ28ኛው እና በ32ኛው ደቂቃ ላይ መኾኑ በመልካም አብነት ይነሳላቸዋል፡፡

ስፖርት ወዳዱ የደሴ እና አካባቢው ማኅበረሰብ እንዲሁም ከተማ አሥተዳደሩ ደግሞ ቡድኑ ወደ ፕሪሚየር ሊግ እንዲገባ ብርቱ ጥረት እና ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ የደሴ ከተማ ነዋሪው መሐመድ ዮናታን ቡድኑን በሞራል ከመደገፍ ባለፈ ለቡድኑ ገቢ ማሠባሠቢያ በተዘጋጀው ሩጫ ላይ ለስምንት ቤተሰቦቼ መልያ በመግዛት አጋርነቴን አሳይቻለሁ ይላሉ፡፡

ሌሎች የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ከቤተሰቦቻቸው ባለፈ ለሌሎችም መሊያውን በመግዛት እንዲደግፉና እንዲያስተዋውቁ አድርጌያሁ፤ ድጋፌም ይቀጥላል ብለዋል፡፡ ተጫዋቾችም ከተማ አሥተዳደሩ ቡድኑን በተለየ ሁኔታ እየደገፈ ነው፤ የማትጊያ ሽልማትም ይሰጣል፤ ቃልም ተገብቶልናል ብለዋል፡፡

የደሴ ከተማ አሥተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ሰይድ አራጋው ለአሚኮ እንዳሉት ከተማ አሥተዳደሩ ለቡድኑ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡ ቡድኑ ከተጫዋቾች ጋር በገባው ውል መሠረት ደመወዛቸው በአግባቡ ከመክፈል ባለፈ በየአንዳንዱ ጨዋታ ሲያሸንፉ የማትጊያ ክፍያም ይደረጋል ነው ያሉት፡፡

ለቡድኑ አቅም መፍጠሪያም የንቅናቄ ሥራ መከናወኑ ተጫዋቾችን እንዳበረታታቸው አቶ ሰይድ ተናግረዋል፡፡ ለስፖርተኞች ምቹ የኾኑ ፋሲሊቲዎች እየተሟላላቸው ነው ያሉት ኀላፊው በተሻለ ሆቴል እንዲያርፉ ስለመደረጉም አብራርተዋል፡፡ በየጨዋታው የነበረው አቋም ባለሙያዎች እየተመደቡ ይገመገማል፤ ግብረ መልስም በመስጠት ውጤቱ እንዲሰምር አስቻይ ሁኔታዎች ተፈጥሯል ብለዋል፡፡

ደሴ ከተማ በከፍተኛ ሊጉ ክስተት ኾኖ የመጣ ተፎካካሪ ቡድን ነው ያሉት መምሪያ ኀላፊው የፊታችን እሑድ ከነገሌ አርሲ ከተማ የሚያደርገውን ወሳኝ ጨዋታ ለማሸነፍ ስለመዘጋጀቱም ጠቁመዋል፡፡ “ጨዋታውን ማሸነፍ ማለት አንድ እግራችንን ወደ ፕሪሚየር ሊግ ማስገባት ማለት ነው“ ብለዋል፡፡

መምሪያ ኀላፊው ቡድኑ መጋቢት 14/2017 ዓ.ም ከነገሌ አርሲ ከተማ ጋር ለሚያደርገው ጨዋታ አቅማቸው የሚፈቅድላቸው የቡድኑ ደጋፊዎች ከየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ወደ አዲስ አበባ በመሄድ ተጫዋቾችን እንዲያበረታቱም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በሙሉጌታ ሙጨ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here