የባሕል ስፖርት ውድድር አሸናፊው ልዑክ አቀባበል ተደረገለት።

0
136

ባሕር ዳር: መጋቢት 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በ22ኛው የባሕል ስፖርት ውድድር እና በ18ኛው የባሕል ፌስቲቫል አሸናፊ የኾነው የአማራ ክልል የልዑካን ቡድን በባሕር ዳር አቀባበል ተደርጎለታል። በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሆሳዕና ከተማ በተደረገው 22ኛው የባሕል ስፖርት ውድድር የአማራ ክልል ስምንት ዋንጫዎችን በመወስድ በበላይነት አጠናቅቋል።

በ11 የስፖርት ዓይነቶች ከተደረገው ውድድር ክልሉ በሰባቱ የስፖርት ዓይነቶች ዋንጫዎችን አሸንፏል። በአጠቃላይ ውድድርም አሸናፊ በመኾን ስምንት ዋንጫዎችን በመውሰድ ነው በበላይነት ያጠናቀቀው። የክልሉ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ኀላፊ እርዚቅ ኢሳ በአቀባበል ሥነ ሥርዓቱ ላይ የስፖርት ልዑካኑ ወደ ወድድር ሲሸኙ አደራ ተሰጥቷቸው እንደነበር አስታውሰዋል።

በባሕል ስፖርት የአማራ ክልል ወደፊትም እጅ የማንሰጥበት ነው፤ ሁልጊዜም አሸናፊ መኾን አለበት ብለን እየሠራን እንገኛለን ነው ያሉት። ለ22ኛ ጊዜ በተደረገው የባሕል ስፖርት ውድድር የአማራ ክልል ስፖርተኞች ለ20 ጊዜ በማሸነፍ አደራቸውን ተውጥተዋል ብለዋል። ክልሉ በችግር ውስጥ ቢኾንም ችግርን ተቋቁመው ማሸነፍ የሚችሉ ትጉህ ልጆች እንዳሉት የሚያመላክት ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ከምዕራብ ጎጃም ዞን የተመረጠችው ትኳደድ አረጋ የሦሥት ወር ሕጻን ይዛ የወርቅ ሜዳሊያ ለክልሏ በማስገኘቷ አቶ እርዚቅ በልዩነት አመሥግነዋታል። ተመስገን ዓለማየሁ የገበጣ ተዋዳዳሪ ነው። “ውድድሩ ፈታኝ ቢኾንም በፍቅር እና በሞራል በመወዳደራችን ማሸነፍ ችለናል” ነው ያለው።

በአቀባበል ሥነ ሥርዓቱ ላይ የክልሉ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፦ ሙሉጌታ ሙጨ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here