ባሕር ዳር: መጋቢት 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የ2024/25 የሻምፒየንስ ሊጉ ጥሎ ማለፍ የመልስ ጨዋታዎች ምሽቱን ተከናውነዋል። ጀርመን፣ እንግሊዝ እና ስፔን እያንዳንዳቸው በሁለት ክለቦች ሲወከሉ፤ ፈረንሳይ እና ጣልያን አንድ አንድ ክለብ ወደ ሩብ ፍፃሜ አሳልፈዋል።
ከጨዋታው አስቀድሞ አሠልጣኝ ዲያጎ ሲሞኔ “አንቼሎቲ ከእኔ በጣም እንደሚሻል ግልጽ ነው” ብለዋል። ውጤቱም ሜዳ ላይ ታይቶ ማሪንጌዎቹ ወደ ሩብ ፍፃሜው ተሻግረዋል። በማድሪድ ደርቢ አትሌቲኮ ማድሪድ በሜትሮፖሊታኖ ስታዲየም ሪያል ማድሪድን ገጥሞ በመደበኛ ሰዓት 1ለ0 አሸንፎታል።
ይህ ተጠባቂ ጨዋታም በኳታር የ2022 የዓለም ዋንጫ የፍፃሜውን ጨዋታ በዳኙት ፖላንዳዊው ዳኛ ሲሞን ማርሲንያክ ተመርቷል። በሁሉም ውድድር ባለፉት ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ሽንፈት የገጠመው ባለሜዳው አትሌቲኮ ማድሪድ ወደ ድል ለመመለስ ቢጫወትም አልተሳካም።
ሁለቱ ክለቦች በሁሉም ውድድር እርስ በርስ ካደረጓቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች አንድ አንድ ጊዜ ድል የቀናቸው ሲኾን በሦስቱ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። የትናንቱ ስድስተኛ ግንኙነት ግን የውጤት የበላይነቱን ከተጨማሪ ደቂቃ አልፎ በመለያ ምቶች አረጋግጧል። በመለያ ምት 4-2 አትሌቲኮ ማድሪድን በማሸነፍም ወደ ሩብ ፍፃሜ ገብቷል።
የፍፁም ቅጣት ምት ሲመታ በሁለቱ እግሮቹ ኳሷን የነካው ጁሊያን አልቫሬዝ በአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር ሕግ 14 መሠረት ያስቆጠረው ግብ እንዲሻር ተደርጓል። በጨዋታው ቁጥራዊ ብልጫ ለነበረው አትሌቲኮም ዕድለኛ ካልነበረባቸው አጋጣሚዎች አንዱ ኾኗል። በተቃራኒው ሪያል ማድሪድ በቻምፒየንስ ሊግ ታሪክ ከየትኛውም ቡድን የበለጠ ለአራት ጊዜያት ያክል በመለያ ምት ተጋጣሚዎቹን መርታት የቻለበት ምሽት ኾኖለታል።
ሪያል ማድሪዶች በመጀመሪያው ዙር ካሸነፉት ያለፉት 23 የቻምፒዮንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ዙር ጨዋታ በ22ቱ ሩብ ፍፃሜ መድረስ ችለዋል። አትሌቲኮ ማድሪድ ከ1997 በኋላ በሜዳው ባደረጋቸው የቻምፒዮንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ሽንፈት ሳይገጥመው ቆይቶ ነበር።
ባለፉት ተከታታይ ሁለት ዓመታት የቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታን በለንደን እያስተናገደ የሚገኘው ብቸኛው ስታድየም ኤምሬትስ፤ ትናንት ምሽትም ፒኤስቪን አስተናግዷል። በመጀመሪያው ዙር ጨዋታ አርሰናል ወደ ኔዘርላንድስ አቅንቶ ተጋጣሚው ፒኤስቪ ላይ ከግማሽ ደርዘን በላይ ጎል በማስቆጠር አሸንፎ መመለሱ ይታወሳል።
የኔዘርላንዱ ክለብ ከአርሰናል ጋር ላደርገው ጨዋታ ትኬቶችን ለገዙ ደጋፊዎቹ ገንዘቡን መልሷል። ክለቡ ባለፈው ሳምንት 7ለ1 ለተሸነፈበት እና ላሳየው ደካማ አቋም ይቅርታ ለመጠየቅ ከ200ሺህ ዩሮ በላይ የትኬት ወጭ ሸፍኗል። ከ3ሺህ በላይ ተጓዥ ደጋፊዎቹ በታደሙት የመልስ ጨዋታም ከሜዳው ውጭ የተሻለ ቡድን ኾኖ ቀርቧል። ሁለት አቻ የተጠናቀቀው ጨዋታ በደርሶ መልስ 12 ግቦች ተቆጥረውበታል።
ሌላኛው በመድረኩ እንግሊዝን የወከለው አስቶንቪላ ከክለብ ብሩዥን ጋር ተጫውቷል። በደርሶ መልስ ጨዋታው ፍፁም የበላይ የነበረው አስቶን ቪላ በድምር ውጤት 6ለ1 ማሸነፍ ችሏል። ቪላ ከ42 ዓመታት በኋላ በተመለሰበት የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ አስደናቂ ግስጋሴውን ቀጥሏል።
ከፒኤስጂ በውሰት ፈርሞ የመጣው ማርኮ አሴንሲዮ በቪላ ፓርክ የደስታ ጊዜ ማሳለፉን ቀጥሎ በምሽቱም ሁለት ግቦችን አስቆጥሯል። በሻምፒዮንስ ሊጉ የመጀመሪያ የቪላ ግቡ ሲኾን በጥር ለክለቡ ከፈረመ በኋላም የፕሪምየር ሊግ እና ኤፍ ኤን ጨምሮ በአጠቃላይ ስድስተኛ ግቡ ነው።
በተደጋጋሚ የዩሮፓ ሊግ ሻምፒዮኑ ስፔናዊው አሠልጣኝ ኡናይ ኤምሬ ክለቡን ወደ አውሮፓ ኀያልነት የመመለስ እቅዳቸውን እየተገበሩ መጥተዋል። የፈረንሳዩ ክለብ ሊል ቦርሲያ ዶርትመንድን በሜዳው ገጥሞ በሽንፈት ከፉክክሩ ተሰናብቷል። በመጀመሪያ ዙር በሲግናል ኤዱና ፓርክ አንድ አቻ የተጠናቀቀው ጨዋታ በዴካትሎን አሬና ቀጥሎ የጀርመኑ ክለብ ለሩብ ፍፃሜ አልፏል። በድምር ውጤት 3ለ1 በማሸነፍ።
በኦፕታ ትንታኔ የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫን ለማሸነፍ ሊቨርፑል ትልቅ ቅድመ ግምት አግኝቶ ነበር። ነገር ግን በተከታይነት የተገመቱት ኢንተር ሚላን፣ ባርሴሎና፣ አርሰናል፣ ሪያል ማድሪድ፣ ፒኤስጂ እና ዝቅተኛ ግምት የተሰጣቸው ክለቦች ለሩብ ፍፃሜው በቅተዋል።
በዚህ የውድድር ዓመት የቻምፒዮንስ ሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዎች በመኾን ራፊንሃ 11፣ ሃሪ ኬን እና ሴርሁ ጉራሲ እኩል 10 ግቦች እየመሩ ነው። ጊኒያዊው የዶርትመንድ አጥቂ ሴርሁ ጉራሲ አፍሪካዊ ተጫዋች ኾኖ በአንድ የቻምፒየንስ ሊግ የውድድር ዓመት 14 የግብ ተሳትፎ በማድረግ የሞ ሳላህን ክብረወሰን ተጋርቷል።
በቀጣይ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎች በአሠልጣኝ ኡናይ ኤምሬ የሚመሩት ቪላዎች ከፈረንሳዩ ክለብ ፒኤስጂ ጋር ተገናኝተዋል። ባየር ሙኒክ ከኢንተር ሚላን፣ ባርሴሎና ከቦሩሲያ ዶርቱመንድ፣ የውድድሩ ታላቅ ክለብ ሪያል ማድሪድ ደግሞ ከአርሰናል ጋር እንደሚፋለም ተረጋግጧል።
የሩብ ፍፃሜው የመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎቹ መጋቢት 30 ይከናወናሉ። በውድድሩ ታሪክ ባየር ሙኒክ 22 ሪያል ማድሪድ 20 እንዲኹም ባርሴሎና 19 ጊዜ ለሩብ ፍፃሜ በመድረስ ቀዳሚ ክለቦች ናቸው።
በአማኑኤል ፀጋዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!