ባሕር ዳር፡ መጋቢት 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ፈረንሳዊ ኮከብ ፖል ፖግባ በጣሊያኑ ጁቬንቱስ አራት የሴሪኤ ዋንጫዎችን አሳክቷል። በሁለት ምዕራፍ በሚከፈለው የማንቸስተር ዩናይትድ ግልጋሎቱም የተለያዩ ክብሮችን አግኝቷል። የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድንን ወክሎም የዓለም ዋንጫን ስሟል።
ከእነዚህ ክብሮች በተጨማሪ ፖግባ ሜዳ ውስጥ በሚያደረገው እንቅስቃሴም ብዙ አድናቂዎችን አትርፏል። ከሜዳ ውጭ ያለው ሕይወቱ በእግር ኳስ በችሎታው ልክ ከፍ እንዳይል አድርጎታል ተብሎ የሚተቸው ፖግባ ለ18 ወራት እግር ኳስ እንዳይጫወት ታግዶ ቆይቷል። እንደ አውሮፓውያኑ መስከረም 2023 አቆጣጠር ተጫዋቹ የተከለከለ አበረታች ነገር መጠቀሙም ተረጋግጧል።
ይህን ተከትሎ ለአራት ዓመታት ከእግር ኳስ ታግዶ ነበር። ነገር ግን ፖግባ ይግባኝ በመጠየቁ ዓለም አቀፉ የስፖርት ገላጋይ ፍርድ ቤት ቅጣቱን ወደ 18 ወራት ቀንሶለታል። ይህ የተጣለበት የ18 ወራት እገዳው ዛሬ መጠናቀቁን ሚትሮን ጨምሮ የተለያዩ የስፖርት ምንጮች አስነብበዋል። ፖግባ ከጁቬንቱስ ጋር ያለው ውል የተቋረጠ ሲኾን ቀጣይ ክለቡንም ገና አላወቀም። በፈረንሳዩ ማርሴ፣ በአሜሪካ ክለቦች እና በጃፓን ክለቦች እየተፈለገም ነው።
ፉትቦል ቡም የተሰኘ የመረጃ ምንጭ እንዳስነበበው ፖግባ በፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ዳግም የመጠራት ህልም አለው። በዚህ ምክንያት በአውሮፓ መጫወትን ቅድሚያ ምርጫው ያደርጋል። ተጫዋቹ ከ2026ቱ የዓለም ዋንጫ በፊት አሳማኝ ብቃት በማሳየት በዓለም ዋንጫው መካተትን አቅዷል ተብሏል።
ማንቸስተር ዩናይትድ ፈረንሳዊውን አማካይ እንደሚፈልገው ሲነገር ቢቆይም አኹን ላይ ግን ወሬው ተቀዛቅዟል። ቀጣይ መዳረሻው የት ይኾናል የሚለው እንዳለ ኾኖ የተረሳው ኮከብ ግን ከዛሬ ጀምሮ ወደ እግር ኳሱ ተመልሷል።
በአስማማው አማረ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!