የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ መድን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል፡፡

0
157

ባሕር ዳር: መጋቢት 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 22ኛ ሳምንት የኢዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ዛሬ ሲቀጥል ሁለት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ፡፡ የመጀመሪያው ጨዋታ 9 ሰዓት የሚካሄድ ሲኾን የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ መድን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው፡፡
ኢትዮጵያ መድን በ38 ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው።

የዛሬው ጨዋታ መሪነቱን ለማጠናከር እና ከተከታዮቹ በብዙ የነጥብ ርቀት ለመምራት የሚያደርገው ጨዋታ ነው፡፡ ኢትዮጵያ መድን በዘንድሮው የፕሪምየር ሊጉ ጨዋታ የተሻለ አቋም እያሳየ የመጣ ቡድን ነው። እስካሁን 19 ጨዋታዎችን አድርጎ ሦስት ጊዜ ብቻ ሲሸነፍ አምስት ጊዜ አቻ በመውጣት 11 ጊዜ ማሸነፍ የቻለ ቡድን ነው፡፡

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ28 ነጥብ በሊጉ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው። በ19 ጨዋታዎች አምስት ጊዜ ሲሸነፍ ሰባት ጊዜ አቻ ወጥቶ ሰባት ጊዜ ደግሞ ድል ቀንቶታል፡፡ ክለቡ በ20ኛ እና በ21ኛ ሳምንት ጨዋታ ላይ ያደረጋቸውን ጨዋታዎች ማሸነፍ መቻሉ የተሻለ ሥነ ልቦና ገንብቷል፡፡
በዛሬው ጨዋታ ላይም ከመሪው ጋር የተሻለ ተፎካካሪ እንደሚኾንም ነው የሚጠበቀው፡፡

ሁለቱ ክለቦች በሊጉ እስካኹን ሰባት ጊዜ የመገናኘት እድል ነበራቸው። በጨዋታቸውም አራት ጊዜ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ደግሞ ኢትዮጵያ መድን አሸንፏል፡፡ ሁለት ጊዜ በተገናኙበት ጨዋታ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡

22ኛ ሳምንት የኢዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ 12 ሰዓት ሲቀጥል ወላይታ ድቻ ከውልዋሎ አዲግራት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡

በምሥጋናው ብርሃኔ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here