በሊጉ የደረጃ ለውጥ የሚያስከትል ጨዋታ ዛሬ ይደረጋል።

0
120

ባሕር ዳር: መጋቢት 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ 28ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ ዌስት ሃም ዩናይትድ እና ኒውካስትል ዩናይትድ በለንደን ስታዲየም ምሽት አምስት ሰዓት ይጫዎታሉ፡፡ በጨዋታው አሸናፊ የሚኾነው ቡድን ደረጃውን ከፍ ማድረግ ያስችለዋል፡፡

ሁለቱ ቡድኖንች ዛሬ ለ145ኛ ጊዜ የሚጫወቱ ይኾናል፡፡ ቀደም ሲል በተገናኙባቸው 144 ጨዋታዎች ደግሞ ኒውካስትል ዩናይትድ በ59 ጨዋታዎች በማሸነፍ የበላይ ነው፡፡ በአንጻሩ ዌስትሀም ዩናይትድ በ44ቱ አሸንፏል፡፡ በ41 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡

በቅርብ በተገናኙበት አምስት ጨዋታዎች ኒውካስትል ዩናይትድ በሁለት ጨዋታዎች በማሸነፍ የበላይ ሲኾን ዌስትሀም ዩናይትድ በአንዱ ድል ነስቷል፡፡ በሁለት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡

በዘንድሮው ፕሪምየር ሊግ ኒውካስትል ዩናይትድ 27 ጨዋታዎችን አድርጓል፡፡ በ13 በማሸነፍ፣ በዘጠኙ በመረታት፣ በአምስቱ አቻ በመለያት 44 ነጥብ ሠብሥቦ ዘጠነኛ ላይ ይገኛል፡፡

ኒውካስትል ዩናይትድ ጨዋታውን ካሸነፈ ደረጃን ከዘጠነኛ ወደ ስድስተኛ ከፍ የሚያደርግ ይኾናል፡፡ የቡድኑ አሠልጣኝ ኤዲ ሀው ወደ ሙሉ አቋሙ እየተመለሰ ያለ ጠንካራ ቡድን እየገነባን ነው ብለዋል፡፡

በዛሬው ጨዋታ በጉዳት ምክንያት የማይሰለፉ ወሳኝ ተጫዋቾች ቢኖሩም ከተጫዋቾች የማሸነፍ ቁርጠኝነትን አይቼባቸዋለሁ፤ በመኾኑም ዌስት ሀምን ለማሸነፍ እንጫወታለን ብለዋል፡፡

ዌስትሀም ዩናይትድ በሊጉ 27 ጨዋታዎችን አድርጎ ያሸነፈው ዘጠኝ ጨዋታዎችን ብቻ ነው፡፡

በ12 ጨዋታዎች ተሸንፎ፣ በስድስቱ አቻ ተለያይቶ በ33 ነጥብ 16ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ቡድኑ የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ ደረጃውን ማሻሻል ያስችለዋል፡፡

የዌስትሀም አለቃ ግርሃም ፖተር ”ጥሩ ልምምድ ሠርተናል፡፡ ተጫዋቾቼም ያላቸው ቤተሰባዊ ስሜት ልዩ ነው፤ የዛሬውን ጨዋታ አሸናፊ ሊያደርጉን የሚችሉ ሥራዎችንም አከናውነናል” ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ሊጉን 29 ጨዋታዎችን ያደረገው ሊቨርፑል በ70 ነጥብ እየመራው ይገኛል፡፡ አርሰናል ከ28 ጨዋታዎች 55 ነጥብ በመያዝ ይከተላል፤ ኖቲንግሃም ፎረስት በ51 ነጥብ በሦስተኛነት ተቀምጧል፡፡

ኢፕስዊች ታዎን፣ሌሲስተር ሲቲ እና ሳውዝአምፕተን ወራጅ ቀጣናው ላይ ይኛሉ፡፡

በሙሉጌታ ሙጨ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here