ተጠባቂው የባሕር ዳር ከተማ እና ሀድያ ሆሳዕና ጨዋታ

0
92

ባሕር ዳር: መጋቢት 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 22ኛ ሳምንት የኢትዮዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ዛሬ ሲቀጥል በደረጃ ሰንጠረዡ ተከታታይ ኾነው የሚገኙት ባሕር ዳር ከተማ እና ሀድያ ሆሳዕና ይገናኛሉ። ይህ ጨዋታ በፕሪምየር ሊጉ ይበልጥ ተፎካካሪ ለመኾን እና የደረጃ ሠንጠረዡን ከሚመሩት ክለቦች ለመጠጋት የሚደረግ ጨዋታ በመኾኑ ትኩረት አግኝቷል።

በዚህ ዓመት የጣና ሞገዶቹ በፕሪምየር ሊጉ ባደረጓቸው 19 ጨዋታዎች ወጥ አቋም ባያሳዩም በቅርቡ ካደረጉት ጨዋታ በመነሳት የተሻለ እንቅስቃሴ እያደረጉ እንደኾነ መገንዘብ ይቻላል። የጣና ሞገዶቹ አኹን ላይ በ30 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኙት። በቅርብ ጨዋታ ቡድኑ ቅዱስ ጊዮርጊስን አሸንፏል። ከፋሲል ከነማ ጋር ደግሞ አቻ መለያየቱ ይታወሳል።

የጣና ሞገዶቹ እስካኹን በፕሪምየር ሊጉ 19 ጨዋታ አድርገው አምስት ጊዜ ሲሸነፉ ስድስት ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። ስምንት ጨዋታዎችን ደግሞ በአሸናፊነት አጠናቀዋል። በሌላ በኩል ተጋጣሚው ሀድያ ሆሳዕና በፕሪምየር ሊጉ በተመሳሳይ ወጥ አቋም የማይታይበት ነው። በፕሪምየር ሊጉ 19 ጨዋታዎችን ያደረገ ሲኾን 32 ነጥብ ሰብስቦ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው።

እስካኹንም ባደረጋቸው ግጥሚያዎች ዘጠኝ ጨዋታዎችን አሸንፎ አምስት ጊዜ ሲሸነፍ አምስት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል። ቡድኑ በቅርብ ያደረጋቸውን ግጥሚያዎች ስንመለከት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያደረገውን ጨዋታ ድል ሲቀናው ከኢትዮጵያ መድን እና ከሀዋሳ ከተማ ጋር ያደረጋቸውን ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ማጠናቀቁ ይታወሳል።

የጣና ሞገዶቹ እና ሀድያ ሆሳዕና እስካኹን 10 ጊዜ በፕሪምየር ሊጉ ተገናኝተው ሁለቱም አራት ጊዜ ድል ሲቀናቸው ሁለት ጨዋታዎች ላይ አቻ ተለያይተዋል። ሁለቱ ቡድኖች ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ በደረጃ ሠንጠረዡ ላይ የሚፈጥረው ለውጥ በመኖሩም ተጠባቂ ያደርገዋል። ጨዋታውም ቀን 9 ሰዓት ላይ ይካሄዳል።

የኢትዮዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ 22ኛ ሳምንት ሲቀጥል 12 ሰዓት ላይ ደግሞ ሲዳማ ቡና ከአዳማ ከተማ ጋር ይገናኛሉ።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here