0
157

ረመዳን እና ሙስሊም የእግር ኳስ ተጨዋቾች
ባሕር ዳር: መጋቢት 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በረመዳን ወር እርዳታ ለሚሹ ሰዎች ድጋፍ ማድረግ የሃይማኖቱ ተከታዮች ከሚያከናውኗቸው ተግባራት ውስጥ አንዱ ነው። መጾም ደግሞ እስላማዊ ግዴታ እና ፈጣሪን መቅረቢያ ሃይማኖታዊ ክዋኔ ነው።
በዓለም ላይ ስመ ጥር ከኾኑት የእግር ኳስ ተጨዋቾች ውስጥ ካሪም ቤንዜማ፣ ሳዲዮ ማኔ፣ ሞሐመድ ሳላህ፣ ኒጐሎ ካንቴ፣ ሪያድ ማህሬዝ፣ አንቶኒዮ ሩዲገር፣ ኢካይ ጉንዶጋን፣ ኦስማን ዴምቤሌ፣ አችራፍ ሀኪም፣ ዌስሊ ፎፋና፣ ፍራንክ ኬሲ፣ ሀኪም ዚያች፣ እስማኤል ሳር፣ ኑሴየር ማዝራዊ እና ሌሎችም የእስልምና ዕምነት ተከታዮች ናቸው።
እነዚህ ስማቸውን የጠቀስናቸው እና ሌሎችም ሙስሊም የእግር ኳስ ተጨዋቾች የረመዳን ወርን “ተወዳጁ ወር” ሲሉ ይገልጹታል።
የዘንድሮዉ የረመዳን ወር ተጀምሮ ቀናት ተቆጥረዋል። እኛም በፊፋ የመረጃ ገጽ ያገኘነውን ሙስሊም ተጨዋቾችን እና ገጠመኞቻቸውን አስመልክቶ ጥቂት መረጃ እናጋራችሁ፡፡
በ2019 እ.ኤ.አ አያክስ አመስተርዳም እና ቶተንሀም ሆትስፐር የቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታቸውን ሲያደርጉ የያኔዎቹ የአያክሶቹ ሐኪም ዚያች እና ኑሴየር ማዝራዊ በጨዋታቸው መካከል የአፍጥር /ጾም መፍቻ/ ሰዓት ሲደርስ ለአጭር ደቂቃዎች ጨዋታቸውን አቋርጠው ጾማቸውን በመፍታት ወደ ጨዋታቸው ተመልሰዋል።
“እኔ ሙስሊም እና ፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ተጫዋች ነኝ” ያለው የቀድሞው የአያክስ፣ የቼልሲ አሁን ደግሞ በጋላታሳራይ የሚገኘው ሞሮኳዊው ሐኪም ዚያች እንደ ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጫዋችነቱ የክለብ ሙያዊ ግዴታውን ከመወጣት ጐን ለጐን በዕምነቱም የጸና አቋም እንዳለው ገልጿል።
እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር በ2021 ክሪስታል ፓላስ ከሌስተር ሲቲ ጋር ባደረጉት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ላይ እንግሊዛዊዉ ዳኛ ግርሃም ስኮት ጨዋታው በ34ኛው ደቂቃ ላይ እንዲቋረጥ ፊሽካቸውን ነፍተዋል። ምክንያታቸዉ ደግሞ የያኔው የሌስተር ሲቲ (የአሁኑ የቼልሲ) ተጫዋች ዌስሊ ፎፋና ‘አፍጥር’ የሚያደርግበት /ጾሙን የሚፈታበት ሰዓት/ በመድረሱ ነው። ዳኛው ጨዋታዉን ባስቆሙበት ፍጥነት ዌስሊ ፎፋና ወደ ሜዳዉ መስመር በመሄድ ጾሙን እንዲፈታ አስችለውታል።
የዳኛ ግርሃም ስኮት ተግባር የክሪስታል ፖላስ እና የሌስተር ሲቲ ደጋፊዎችን ምስጋና አስገኝቶላቸዋል። በርካታ ሙስሊም የኾኑ እና ያልኾኑ ተጫዋቾችም ለዳኛው አድናቆታቸውን አቅርበዋል። በዕለቱ ከዳኛዉ ፍቃድ አግኝቶ ጾሙን የፈታዉ ዌስሊ ፎፋናም የእግር ኳስ ተጫዋቾች፣ ደጋፊዎች፣ አሠልጣኞች እና ዳኞች ለሃይማኖቱ የሰጡትን ክብር ከልቡ አመስግኗል።
ሩሲያ ባዘጋጀችው የ2018 እ.ኤ.አ የዓለም ዋንጫ በትዝታ ስንጓዝ ደግሞ የቱኒዚያ ብሔራዊ ቡድን ከፖርቹጋል እና ከቱርክ ጋር ባደረጉት ጨዋታ ሙስሊም ተጫዋቾች የጾም መፍቻ ሰዓታቸው /የአፍጥር ጊዜያቸው/ ሲደርስ የቱኒዚያው ግብ ጠባቂ ሙኤዝ ሀሰን በፈጠረው ዘዴ ጨዋታው ሳይቋረጥ ወይም ዳኛው ፍቃድ ሳይሰጡ ጿሚዎች ፆማቸውን እንዲፈቱ ማድረግ ችሏል።
የቱኒዚያው ግብ ጠባቂ ሙኤዝ ሀሰን ቱኒዚያ ከፖርቹጋል ጋር እየተጫወተች ባለችበት ወቅት የአፍጥር ሰዓት መድረሱን ጠብቆ በእግሩ ላይ ጉዳት የደረሰበት በማስመሰል ዳኛው ሐኪሞች ገብተው እንዲረዱት ትዕዛዝ እንዲያስተላልፉ አስገድዷቸዋል። ከቱርክ ጋር ሲጫወቱ ደግሞ ትከሻዉ ላይ ጉዳት ያጋጠመዉ አስመስሎ ዳኛው የሕክምና አባላትን ወደ ሜዳ ለመግባት እንዲያዝዙ የተለመደ ዘዴዉን ተጠቅሟል።
ግብ ጠባቂው ሙኤዝ ሀሰን ሜዳ ላይ እየወደቀ የሐኪሞችን እርዳታ በሚያገኝበት ወቅት የቱኒዚያ እና የተፋላሚያቸው ሙስሊም ተጫዋቾች አፍጥር ያደርጋሉ። በሙኤዝ ሀሰን ቅን ተንኮል ጾማቸውን የሚፈቱት ግን ተጫዋቾች ብቻ ሳይኾኑ ሙስሊም የኾኑ የአሠልጣኝ ቡድን አባላት እና ሌሎችም ባለሙያዎች ጭምር ናቸው።
የግብ ጠባቂዉ ዘዴ ሕግ ያልወጣለትን የሙስሊም ተጫዋቾች የማፍጠሪያ ጊዜ በዘዴ ያስገኘ ኾኖ በወቅቱ ሰፊ የዘገባ ሽፋን ተሰጥቶታል።
የረመዳን ወር ለሙስሊም ተጫዋቾች ከአካል ብቃት ጋር ተያይዞ የሚፈትናቸዉ መኾኑ ይታወቃል። ያም ኾኖ ግን አብዛኞቹ ሙስሊም የእግር ኳስ ተጫዋቾች አካላዊ ድካማቸው በጾማቸዉ ከሚያገኙት መንፈሳዊ እርካታ ጋር እንደማይነጻጸር ይገልፃሉ። እርካታቸው ይበልጣልና።
በ2021 እ.ኤ.አ አብዛኛዎቹ የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ተጫዋቾች ከአምበሎች ጋር በመነጋገር የማፍጠሪያ ሰዓት ከደረሰ ኳስ በእጅ ሊወረወር ወይም ከማዕዘን ሊሻማ ሲል ጾማቸውን የሚፈቱ ሙስሊም ተጫዋቾች ጾማቸውን እንዲፈቱ ኳስ ወርዋሪው ወይም ማዕዘን ምት መቺው አውቀው ኳስ እንዲያዘገዩ ስምምነት ፈጽመዋል።
በዚህም መሠረት ሙስሊም ተጫዋቾት ኳስ በእጅ ሊወረወር ሲል እና ከማዕዘን ሊሻማ ሲል በፍጥነት ጾማቸውን ፈትተዉ ወደ ጨዋታቸው ይመለሳሉ።
ባለፉት ዓመታት የሊቨርፑል የውጤት መሠረት የኾኑት ሳዲዮ ማኔ እና ሞሐመድ ሳላህ በረመዳን ወርም ክለባቸውን በትጋት አገልግለዋል። ይህንን የተረዱት የቀዮቹ አሠልጣኝ የነበሩት የርገን ክሎፕ ለሁለቱ ሙስሊም ተጫዋቾቻቸውም ኾነ ለሌሎቹ የዕምነቱ ተከታዮች ሁለት እና ሦስት ደቂቃዎችን ለአፍጥር መፍቀድ የሚጠይቀው ቅንነትን ብቻ ስለመኾኑ ገልጸዋል።
አሁን ላይ ምንም እንኳን ሞሐመድ ሳላህ በሊቨርፑል መለያ ደማቅ ታሪክ እየጻፈ ቢኾንም የቀድሞው አሠልጣኙ የርገን ክሎፕ እና አጣማሪው ሳዲዮ ማኔ ግን በክለቡ አብረውት አይገኙም።
ሙስሊም የእግር ኳስ ተጨዋቾች በማፍጠሪያ ሰዓታቸው የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ወይም በዳኞች ይኹንታ ጾማቸውን የሚፈቱበት ጊዜ አሁን ላይ አብቅቷል። ምክንያቱም የእግር ኳስ አሥተዳዳሪው (ፊፋ) የማፍጠሪያ ሰዓት ሲደርስ ጨዋታዎች ተቋርጠው ማፍጠር እንዲችሉ ፈቅዷልና ነው።
በቅርቡ ማንቸስተር ዩናይትድ ከፉልሃም ጋር ባደረጉት የጥሎ ማለፍ ጨዋታ የማንቸስተር ዩናይትዱ ማዝራዊ ጾሙን እንዲፈታ ጨዋታው ለአምስት ደቂቃ ተቋርጦ ነበር። ይህም የአዲሱ የፊፋ ሕግ አካል ነው።
ዘጋቢ፡- እሱባለው ይርጋ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here