እኔም እችላለሁ!

0
131

ባሕር ዳር: የካቲት 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በየዘርፉ ምሳሌ የሚኾኑ ሴቶች በየታሪክ እጥፋቱ ብቅ ብቅ ማለታቸው አልቀረም። በተለይም ለሴቶች የማይቻሉ ያልተፈቀዱ የሚመስሉ እና እንደዛም ተደርገው የሚወሰዱ በርካታ የሥራ መስኮች አሉ። እነዚህን የሥራ መስኮች ግን እነዚህ ሴቶች ሠርተው እና ኾነው፣ ውጤትም አምጥተው አሳይተውበታል።

እንዲህም ይቻላል ያስባሉ ከወንዶች ባልተናነሰም አንዳንዶቹም በበለጠ ሠርተው በማሳየት የይቻላልን መንፈስ ለተከታዮቻቸው በማሳየት አርዓያ የኾኑት ብዙ ናቸው። በተለይም ለወንዶች ብቻ የተፈቀደ እስኪመስል በማኅበረሰቡ ባልተፈቀደው የእግር ኳስ ዘርፍ የሀገራችን የሴት ፈርጦች ብዙ ቢኾኑም ዛሬ የእግር ኳሱ ፈርጥ የኾነችውን ሎዛ አበራን የስኬት ጉዞ እንቃኛለን።

ሎዛ አበራ የተወለደችው በዱራሜ ከተማ ነው። በልጅነት ጊዜዋ ልክ እንደሌሎቹ ሴቶች የማኅበረሰብ ጫና ቢኖርባትም ይህን ጫና በመቋቋም የምትወደውን ኳስ በቀየዋ ታንከባልል እንደነበር ይነገራል። ከፍ እያለች ስትመጣ የእግር ኳስ ሕይወቷን ከሀዋሳ ከተማ የጀመረችው ሎዛ በመቀጠልም በደደቢት፣ በአዳማ እና በውጭ ሀገራትም ተጫውታለች።

በውጭ ሀገራትም በሆላንድ ክለቦች የሙከራ ጊዜን አሳልፋለች፤ በማልታው ቢርኪርካራ ደግሞ ስኬታማ ቆይታ ማድረግ የቻለች ድንቅ ተጫዋች ናት። በአሜሪካ ቨርጂኒያ ማራውደርስ እና ዲሲ ፓወር በተባሉ ክለቦች ተጫውታ ችሎታዋን አሳይታለች። አሁን ላይ ለንግድ ባንክ እና ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ትጫወታለች።

በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅናን ያተረፈች የእግር ኳስ ተጫዋች ስትኾን፣ በተለይም በሴቶች ስፖርት ላይ ያላት ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው። እ.ኤ.አ በ2020 በቢቢሲ የዓለማችን 100 ተጽዕኖ ፈጣሪ ሴቶች ዝርዝር ውስጥ መካተት የቻለች ኢትዮጵያዊትም ናት። ሎዛ አበራ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን ተጫዋች ስትኾን በአጥቂነት ቦታ ላይ ትጫወታለች፣ እየተጫወተችም ትገኛለች።

ሎዛ አበራ በተለያዩ ክለቦች በመጫወት ድንቅ የሚባሉ ግቦችን አስቆጥራለች። በተለያዩ የውድድር መድረኮች ኮከብ ግብ አግቢ መኾን የቻለች ተጫዋችም ናት። በአውሮፓ ቆይታዋ የተለያዩ የሊግ ዋንጫዎችን አሸንፋለች። በእግር ኳስ ሕይወቷ በተለያዩ ጊዜያት ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት እና የምርጥ ተጫዋችነትን ክብር ማግኘት የቻለች ምርጥ ተጫዋችም ናት።

በአውሮፓ ቆይታዋ የተለያዩ የሊግ ዋንጫዎችን በማሸነፍ ለሀገሯ ልጆች አርዓያ እና የሞራል ስንቅ መኾን የቻለች ተጫዋችም ናት። ቢቢሲ፣ ቪኦኤ እና ኢቢሲ የመረጃ ምንጮቻችን ናቸው።

ዘጋቢ:- ምሥጋናው ብርሃኔ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here