ባሕር ዳር: የካቲት 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የ21ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ዛሬ ሲቀጥሉ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ኢትዮጵያ መድን ከድሬዳዋ ከተማ እና መቻል ከወልዋሎ አዲግራት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ኢትዮጵያ መድን በ35 ነጥብ የደረጃ ሠንጠረዡን እየመራ ነው። ዛሬው ጨዋታም መሪነቱን ለማጠናከር ወሳኝ ነው።
ክለቡ ምንም እንኳ ፕሪምየር ሊጉን ቢመራም በቅርብ ጨዋታዎች ወጥነት የጎደለው እንቅስቃሴ ውስጥ ነው።
በተለይም በቅርቡ ካደረጋቸው ሦስት ጨዋታዎች ውስጥ ሁለት ጊዜ ተሸንፎ አንድ ጊዜ ነው ያሸነፈው።
ተጋጣሚው ድሬዳዋ ከተማ በበኩሉ በደረጃ ሠንጠረዡ በ21 ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ነው። ክለቡ ደካማ የሚባል ወቅታዊ አቋም ያለው ሲኾን ባለፉት ሦስት ጨዋታዎችም አንድ ጊዜ ተሸንፎ ሁለት ጊዜ አቻ ወጥቷል።
በዚህ ጨዋታም የኢትዮጵያ መድን የማሸነፍ ቅድመ ግምትን አግኝቷል።
ሁለቱ ክለቦች አምስት ጊዜ ተገናኝተው ሦስት ጊዜ የኢትዮጵያ መድን ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ ደግሞ ድሬዳዋ ከተማ አሸንፏል። ጨዋታቸውም 12 ሰዓት ይካሄዳል።
መቻል ከውልዋሎ አዲግራት የሚያደርጉት ጨዋታ ሌላው ትኩረት ያገኘ የፕሪምየር ሊጉ ጨዋታ ነው። ይህ ጨዋታ ቀን 9 ሰዓት ይካሄዳል።
ዘጋቢ:- ምሥጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!