ጎንደር: የካቲት 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ስፖርት ለሰላም፣ ሰላም ለስፖርት” በሚል መሪ መልዕክት የተካሄደው 9ኛው የመላው የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ስፖርታዊ ውድድር የፍጻሜ ዝግጅት ዛሬ እየተካሔደ ነው፡፡ ውድድሩ በላይ አርማጭሆ ወረዳ ትክል ድንጋይ ከተማ ለ11 ቀናት ሲካሄድ መቆየቱ ይታዎሳል።
በውድድሩ ማጠናቀቂያ መርሐ ግብር ላይ የአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጋሻው አስማሜ፣ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ፋሲል ሰንደቁን ጨምሮ ሌሎች የዞን እና የወረዳ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
የአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጋሻው አስማሜ የስፖርታዊ ውድድሩ ውጤታማነት ለሰላም ዘብ የቆመ ማኅበረሰብ ያለበት አካባቢ መኾኑን ማሳያ ነው ሲሉ ተናግረዋል። ተወዳዳሪዎቹ ላይ አርማጭሆ ወረዳ ያላትን የሰላም ተሞክሮ ለመጡበት አካባቢ ማንፀባረቅ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ድግስ መለሰ “ስፖርት ለሰላም፣ ሰላም ለስፖርት” በሚል መሪ መክዕክት የተካሄደው ዞናዊ ውድድር በ11 ስፖርታዊ የውድድር ዓይነቶች ከ800 በላይ ስፖርተኞችን ያሳተፈ መኾኑን ገልጸዋል።
በመርሐ ግብሩ 13 ወረዳዎች እና ሁለት ከተማ አሥተዳደሮች የተሳተፉበት መኾኑን በማንሳት ውድድሩ ተተኪዎችን ለማፍራት ያስቻለ መኾኑን ገልጸዋል። በቀጣይ ለሚካሄደው ለመላው አማራ ስፖርታዊ ውድድር ተሳታፊ ስፖርተኞች መመረጣቸውም ተገልጿል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ፋሲል ሰንደቁ ወረዳው ስፖርታዊ ውድድሩ ውጤታማ እንዲኾን ላበረከተው አስተዋፅኦ አመስግነዋል። በስፖርታዊ ውድድሩ ሂደት የወረዳው እንግዳ ተቀባይነት ባሕል የታየበት መኾኑንም ተናግረዋል።
የላይ አርማጭሆ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ አስረሳው ደሴ ለውድድሩ ስኬታማነት ዝግጅት ሲያደርጉ መቆታቸውን አንስተው ውድድሩ ሰላም፣ ፍቅር እና መተባበር የታየበት መኾኑን ገልጸዋል። ስፖርተኞች ላሳዩት ስፖርታዊ ጨዋነትም አመስግነዋል።
ስፖርታዊ ጨዋነት በተሞላበት መልኩ የተካሄደ ውድድር መኾኑን የገለጹት ተሳታፊዎቹ በውድድር ሂደቱ ልምድ እንደቀሰሙበትም ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- ቃልኪዳን ኃይሌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን