የትናንት ምሽት የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ክስተቶች፦

0
115

ባሕር ዳር: የካቲት 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) -ሊቨርፑል “እድለኛ ” በነበረበት ጨዋታ ፒኤስጂን አሸንፏል።

-በስተመጨረሻም ዣቢ አሎንሶ ለባየር ሙኒክ እጁን ሰጥቷል።

-በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ጥሎ ማለፍ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎች ኢንተር ሚላን እና ባርሴሎናም በድል ተመልሰዋል።

ሊቨርፑል የፒኤስጂን ተከታታይ 22 ጨዋታዎች የማሸነፍ ግስጋሴ ገትቷል።

ለተከላካዮች ራስ ምታት የኾነው ኦስማን ዴምቤሌ፣ ወጣቱ የመስመር አጥቂ ብራድሊ ባርኮላ እና ሌላኛው የመስመር ተጫዋች ቪቻ ክቫርሽኬሊያ ድንቅ ጥምረት ምርጥ ጨዋታን ቢያስመለክትም ቡድናቸው ፔዤን ከሽንፈት መታደግ ሳይችል ቀርቷል።

ፒኤስጂ በዚህ የውድድር ዓመት ከፕሪምየር ሊግ ክለቦች ጋር ሦስት ጊዜ ተገናኝቶ ማንቸስተር ሲቲን ማሸነፍ ችሎ ነበር። አርሰናል እና ሊቨርፑል ግን የውጤት የበላይነት ወስደውበታል።

የወቅቱ የአውሮፓ ምርጥ አጥቂ መሐመድ ሳላህ በትናንቱ ጨዋታ 0 ጎል፣ 0 የግብ ዕድል፣ 0 ሙከራ እና ሌሎች ደካማ ክብረ ወሰኖችን ያስመዘገበበት ምሽትም ኾኖ አልፏል። በጨዋታው አልነበረም ማለት ይቻላል።

10 ለግብነት የቀረቡ ኳሶችን ያዳነው ግብ ጠባቂው አሊሰን ቤከር በአንፃሩ የጨዋታው ኮከብ ኾኖ ተመርጧል። ሊቨርፑል ዘንድሮ በቻምፒዮንስ ሊጉ ከዘጠኝ ጨዋታ ስምንቱን አሸንፏል።

ባየር ሙኒክን ገጥሞ ተሸንፎ የማያውቀው ስፔናዊው አሠልጣኝ ዣቢ አሎንሶ ለመጀመሪያ ጊዜ በሙኒክ ተሸንፏል። አሎንሶ ከስድስት ጨዋታ ሦስት ድል እና ሦስት አቻ ውጤቶችን በመያዝ እስከ ትናንት ምሽት ድረስ የበላይ ነበር። በምሽቱ ጨዋታ ግን ሦስት ለባዶ ተሸንፏል።

ዘንድሮ ለሙኒክ 30 ጎሎች ያስቆጠረው ሃሪ ኬን ትናንትም ሁለት ግቦችን ማስቆጠር ችሏል። የጨዋታው ኮከብ ተብሎም ተመርጧል። የግብ ኳስ ማመቻቸት የቻለው ማይክል ኦሊሴ በበኩሉ ዘንድሮ ለሙኒክ 13 ጎል እና 13 የግብ አስተዋፅኦ አድርጓል። ባየር ሙኒክ እና ባየር ሊቨርኩሰን በቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ የተገናኙት ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ኢንተር ሚላን ከፌይኖርድ ጋር ያደረገውን ጨዋታ 2ለ0 በኾነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።

አርጀንቲናዊው ተጫዋች ላውታሮ ማርቲኔዝ በ18 ግቦች የኢንተር ሚላን የምንግዜም የቻምፒየንስ ሊግ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ መኾን ችሏል፤ የታሪካዊው ተጫዋች ሳንድሮ ማዞላን የ17 ግቦች ክብረወሰን በማሻሻል።

ኔራዙሪዎቹ በቻምፒዮንስ ሊጉ ባደረጓቸው ዘጠኝ ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ተቆጥሮባቸዋል። የቀድሞው የአርሰናል፣ ማንችስተር ዩናይትድ እና ኔዘርላንድ ብሔራዊ ቡድን አጥቂ ሮበን ቫንፐርሲ የመጀመሪያ የቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታውን በአሠልጣኝነት መርቶ ተሸንፏል።

ባርሴሎና ከ70 ደቂቃ በላይ በ10 ተጫዋቾች ተጫውቶ ከሜዳው ውጪ ወሳኝ ድል አሳክቷል። የድል ግቧ አስቆጣሪ ሪፊንሃ ከፈርሚንሆ እና ካካ በመቀጠል በአንድ የውድድር ዓመት በቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ 13 ግብ እና የግብ ዕድሎችን መፍጠር የቻለ ብራዚላዊ ኾኗል።

ባርሴሎናዎች ባለፉት 16 ጨዋታ አንድም ሽንፈት አልገጠማቸውም፤ 13 ድል እና ሦስት አቻ ውጤቶችን አቻ አጠናቅቀዋል።

አሠልጣኝ ሀንሲ ፍሊክ በባየር ሙኒክ እና ባርሴሎና ከ27 ጨዋታዎች 23ቱን በማሸነፍ በሊጉ ቀዳሚው አሠልጣኝ ናቸው።

የሻምፒዮንስ ሊጉ የመልስ ጨዋታዎች በሚቀጥለው ሳምንት ማክሰኞ እና ረቡዕ ይከናወናሉ።

ዘጋቢ:- አማኑኤል ፀጋዬ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here