ባሕር ዳር: የካቲት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 22ኛው የኢትዮጵያ ባሕል ስፖርቶች ውድድር እና 17ኛው የባሕል ፌስቲባል በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሆሳዕና ከተማ የፊታችን የካቲት 29/2017 ዓ.ም ይጀምራል፡፡
በባሕል ስፖርት ለ19 ዓመታት በበላይነት ማጠናቀቅ የቻለው የአማራ ክልል ዘንድሮም አሸናፊነቱን ለማስቀጠል መዘጋጀት አለባችሁ ብለዋል የክልሉ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ኀላፊ እርዚቅ ኢሳ፡፡
ክልሉ ባለፈው ዓመት ለ19ኛ ጊዜ ሻምፒዮን ሲኾን ከዋንጫዎቹ በተጨማሪ የጸባይ ዋንጫ አሸናፊ ነበር። ዘንድሮም የሁሉንም ክልሎች ተወዳዳሪዎች በማክበር በስፖርታዊ ጨዋነት ማጠናቀቅ አለባችሁ ብለዋል ኀላፊው፡፡
የክልሉ ልዑካን ሽኝት ሲደረግላቸው የተገኙት በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) ሌሎች ተወዳዳሪዎች ጠንክረው ስለሚመጡ የአሸናፊነት ታሪካችሁን ለማስቀጠል በተሻለ የሥነ ልቦና ዝግጅት ማድረግ አለባችሁ ብለዋል፡፡
“የባሕል ስፖርታችን ለጠንካራ ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን” በሚል መሪ መልዕክት በሚካሄደው የባሕል ስፖርት ውድድር እና ፌስቲባል ላይ አማራ ክልል በ10 የስፖርት ዓይነቶች እና በ97 ስፖርተኞች ይወከላል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!