ባሕር ዳር: የካቲት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የጥሎ ማለፋ ጨዋታዎች ትናንት ምሸት ጀምሮ እየተካሄዱ ነው። ተጠብቆ የነበረው የማድሪድ ደርቢ በሪያል ማድሪድ አሸናፊነት መጠናቀቁም ይታወሳል። ዛሬም ጨዋታዎች ሲቀጥሉ የፈረንሳዩ ፒኤስጅ ከሊቨርፑል እና የጀርመኖቹ ባየር ሊቨርኩሰን እና ባየር ሙኒክ እርስ በእርስ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች በጉጉት ይጠበቃሉ።
የፓሪሰን ጀርሜ እና ሊቨርፑል የዛሬ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ፈረንሳይ ላይ ነው የሚካሄደው። ሁለቱ ክለቦች በሀገር ውስጥ ውድድሮቻቸው የየሊጎቹ መሪ ናቸው። ወጥ በኾነ ብቃትም ለዋንጫ እየተቃረቡ ነው። በአውሮፓ መድረክ ውጤታማ ለመኾንም እርስ በእርስ ተፋጥጠዋል። የፒኤስጅው አሠልጣኝ ሊዊስ ሄነሪኬ ሊቨርፑልን ይሄ ጎደለው የማይባል ሙሉ ቡድን ነው ሲሉ ከጨዋታው በፊት ተጋጣሚያቸውን አድንቀዋል።
በአንጻሩ የሊቨርፑሉ አርኒ ስሎት አኹንም የአውሮፓ ምርጡ ክለብ ሪያል ማድሪድ ነው ብለዋል። ክለባቸው የአውሮፓ ምርጥ ለመባልም የሻምፒዮንስ ሊጉን ዋንጫ ማንሳት አለበት ሲሉ አክለዋል። በሊቨርፑል በኩል ኮዲ ጋክፖ ለጨዋታው በጉዳት ብቁ አለመኾኑንም ስሎት ገልጸዋል። ሁለቱ ክለቦች ካላቸው ወቅታዊ ጥሩ ብቃት በተጨማሪ በግለሰብ መሀመድ ሳላህ እና ኦስማን ደንበሌ ምርጥ ዓመትን እያሳለፉ ነው። ዛሬ እና በመልሱ ጨዋታ ለቡድናቸው የሚያደርጉት እገዛም ይጠበቃል።
ሌላኛው የምሽቱ ትልቅ ግምት ያገኘው ጨዋታ ባየር ሙኒክ ባየር ሊቨርኩሰን በሜዳው የሚያስተናግድበት ጨዋታ ነው። በስፔናዊ ዣቬ አሎንሶ እየተመራ በቦንደስ ሊጋው ከዓመታት በኋላ ሙኒክን ከዋንጫ አፈናቅሎታል ሊቨርኩሰን። በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ በደርሶ መልስ ሁለቱ ቡድኖች የሚያደርጉት ጨዋታም ይጠበቃል።
ቤኔፊካ ከባርሴሎና እና ፌኔርድ ከኢንተርሚላንም ሌሎች የዛሬ ጨዋታዎች ናቸው። የቤኔፊካ እና ባርሴሎና ጨዋታ ምሽት 2:30 ሲጀምር ሌሎቹ ምሽት 5 ሰዓት ይካሄዳሉ።
በአስማማው አማረ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!