የዩናይትድ ደጋፊዎች የተቃውም ቀጠሮ

0
115

ባሕር ዳር: የካቲት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ማንቸስተር ዩናይትድ በእንግሊዝም ይሁን በአውሮፖ ገናና ስም የገነባ የእግር ኳስ ክለብ ነው። ነገር ግን ይሄ ኃያልነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸረ ግርማውም እየቀቀለለ መጥቷል።

ከውጤታማው አሠልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ጡረታ በኋላ የክለቡን ኃያልነት እንዲያስቀጥሉ ኦልድትራፎርድ የደረሱ ሁሉ ከታሰቡት በታች ኾነው ተሰናብተዋል።

ተረኛው እና ተስፋ ተጥሎባቸው ቴንሃግን የተኩት ፖርቱጋላዊ አሞሪምም ቴንሃግን የሚያስናፍቁ ኾነው ታይተዋል እስካሁን።

ማንቸስተር ዩናይትድ በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ከመሪው ሊቨርፑል በ34 ነጥብ አንሶ 15ኛ ደረጃ ላይ ተገኝቷል። ባለፉት ዓመታት ለክለቡ ደጋፊዎች የዓይን መመለሻ በነበረው የኤፍኤ ካፕ ዋንጫም ከውድድር ውጭ ኾኗል።

እንዲህ ከጊዜ ወደ ጊዜ መንሸራተቱ የክለቡን ደጋፊዎች እንቅልፍ ነስቷል። በተለይ የክለቡ ባለቤት በኾኑት የግሌዘር ቤተሰቦች ላይ ትልቅ ቂም ይዘዋል። ክለቡ በሜዳ እና ከሜዳ ውጭ ለደረሰበት ውድቀት አሜሪካውያን ባለሃብቶችን በቀዳሚነት ይኮንናሉ።

በዚህ ሳምንትም ደጋፋዎቹ የግለዜር ቤተሰቦች ላይ ተቃውሞ ለማቅረብ የማይቀርበት ቀጠሮ ይዘዋል። የተቃውሞ ቀኑ በትክክል ባይገለጽም ክለቡ በፕሪምየር ሊጉ ከአርሰናል ጋር ከሚያደርገው የእሁዱ ጨዋታ በፊት እንደሚኾን ሚረር አስነብቧል።

ደጋፊዎቹ ጥቁር መለያ በመልበስ ክለቡን እየመሩ ባሉት አካላት እና ባለሀብቶች ላይ ተቃውሟቸውን ያሰማሉ ተብሏል።

ደጋፊዎቹ ከዚህ በፊትም በተደጋጋሚ ተቃሟቸውን አሰምተዋል።

በአስማማው አማረ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here