ባሕር ዳር: ጥር 9/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ቀን 11 ሰዓት ኢኳቶሪያል ጊኒ ከጊኒ ቢሳው በስታድ ኦሊምፒክ አላሳን ኦውታራ ይጫወታሉ፡፡ በመክፈቻው ዕለት በኮትዲቯር የተረታችው ጊኒ ቢሳው ዛሬ ከተሸነፈች በ11 የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎች ላይ ሳታሸነፍ የመውጣትን አስከፊ የእግር ኳስ ታሪኳን ትደግመዋለች፡፡ ከ11 ጨዋታዎች በስምንቱ ግብ አለማስቆጠሯ ደግሞ ድክመቷን ይበልጥ የሚያሳይ ይኾናል፡፡
በአፍሪካ ዋንጫ ዛሬ ኢኳቶሪያል ጊኒ እና ጊኒ ቢሳው የሚያደርጉት ጨዋታ የመጀመሪያቸው በመኾን በታሪክ መዝገብ ይከተባል፡፡ ኢኳቶሪያል ጊኒ ከናይጄሪያ ጋር በመጀመሪያው ዙር ባደረገችው ጨዋታ አንድ ነጥብ ተጋርታለች፡፡ በጨዋታውም ባሳየችው ጠንካራ እንቅስቃሴ ጊኒ ቢሳውን ዛሬ ታሸንፋለች የሚሉ መረጃዎች እየወጡ ናቸው፡፡
ይህንንም የእግር ኳስ ውጤት አስቀድሞ በሚተነብየው ኦፕታ ሱፐር ኮምፒዩተር ደግሞታል፡፡ “ጨዋታውን ኢኳቶሪያል ጊኒ 39 ነጥብ 4 በመቶ ታሸንፋለች” በማለት ገምቷል፡፡
የ34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅ ኮትዲቯር ከናይጄሪያ ከምድብ አንድ ይጫወታሉ፡፡
ይህ የምዕራብ አፍሪካ “ትልቁ የእግር ኳስ ጨዋታ ነው” ተብሏል፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ጨዋታውን “ከምዕራብ አፍሪካ ቀጣና የሁለት ሀገራት የእግር ኳስ ፍጥጫ” ሲሉ እየጠሩት ይገኛሉ፡፡
ለናይጄሪያዊያን “ንሥሮቹ” ጨዋታውን ማሸነፍ በእጅጉ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ናይጄሪያ ዛሬ ሦስት ነጥብ ካላት ሀገር ጋር እንደመጫወቷ ካላሸነፈች ስጋት ላይ መውደቋ አይቀርም፡፡ ንሥሮቹ የዝኾኖቹን ሽኾና በማቁሰል እና እንቅስቃሴያቸውን በመገደብ ግብ ማስቆጠር ብቻ የማለፍ ተስፋቸውን ያለመልመዋል፡፡
ንሥሮቹ የውድድር መክፈቻቸውን 1ለ1 በኾነ ውጤት በተለያዩበት ጨዋታ ወደ ግብ ካሻሟቸው 17 ኳሶች ሰባቱ ብቻ ዒላማቸው ላይ ደርሰዋል፡፡ ከእነዚህ ሙከራዎች ውስጥ ደግሞ ኦሲምሄን ብቻውን ስድስቱን አስቆጥሯል፡፡ እናም ቡድኑ በዚህ ጉምቱ ተጫዋች ላይ ተስፋ አሳድሯል፡፡ ነገርግን ተጋጣሚዋ ኮትዲቯር በደጋፊዋ ፊት እንደመጫወቷ በቀላሉ እጅ ትሰጣለች ተብሎ አይጠበቅም፡፡
ዝሆኖቹ ኮትዲቯራዊያን በመክፈቻው ጨዋታ ጊኒ ቢሳውን 2 ለ 0 በኾነ ውጤት አሸንፈዋል። ባለፉት አምስት ጨዋታዎችም በአራቱ አሸንፈው አንድም ጨዋታ አልተሸነፉም።
ይህን የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ በአሸናፊነት መጀመራቸው ደግሞ በሁሉም ውድድሮች ያሳለፉትን ያለመሸነፍ ጉዞ ሰባት ማድረሳቸው በራስ የመተማመን ሥነ ልቦናቸውን ከፍ ያደርጋሉ ተብሎ ተጠብቋል ሲል ኢቪኒንግ ስታንዳርድ በድረ ገጹ አሰነብቧል፡፡
ዝሆኖቹ በአፍሪካ ዋንጫ ያጋጠሟቸው የመጨረሻዎቹ ሁለት ሽንፈቶች በፍፁም ቅጣት ምቶች የተመዘገቡ ናቸው፡፡ ስለኾነም ተጫዋቾች ፍፁም ቅጣት ክልል ውስጥ ምንም ዓይነት ጥፋት እንዳይሠሩ ተመክረዋል ነው የተባለው፡፡
በ2023 የአፍሪካ ዋንጫ በሁለተኛው ዙር በሁለተኛው ምድብ ግብጽ ከጋና በስታድ ፌሊክስ ኾፑት-ቦይኒ ስታዲየም ምሽት 5:00 ይጫዎታሉ፡፡እስካሁን ሁለቱ ቡድኖች በሁሉም ውድድሮች 23 ጊዜ ተገናኝተዋል። ግብጽ በ12 ጨዋታዎች በማሸነፍ እና በስድስቱ አቻ በማጠናቀቅ በበላይነት ትመራታለች፡፡ ጋና ደግሞ በአምስት ጨዋታዎች ረትታለች፡፡
ግብጽ በ2010 በአፍሪካ ዋንጫ ከጋና ጋር ባደረገችው የፍፃሜ ጨዋታ 1ለ 0 አሸንፋለች፡፡ በ2017 የምድብ ጨዋታም 1 ለ 0 ረትታለች። ቡድኖቹ ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት በ2018 የፊፋ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ሲኾን በጨዋታውም 1ለ1 ተለያይተዋል፡፡
ግብጽ ካለፉት 20 የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ጨዋታዎች በአንዱ ብቻ በናይጄሪያ 1ለ 0 ሽንፈትን አስተናግዳለች።ግብጽ በውድድሩ የመክፈቻ ጨዋታ ከሞዛምቢክ ጋር 2 ለ 2 በኾነ ውጤት በመለያየቷ ዛሬ ወደ ሜዳ ስትገባ በከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ ገብታ መኾኑን ዴይሊ ሜይል አስነብቧል፡፡
ፈርኦኖቹ ከተናዳፊ እባቦች ጋር ሲጫወቱ ሙስታፋ መሐመድ እና መሐመድ ሳላህ ተናበው በመጫወታቸው ነው ነጥብ የተጋሩት፡፡ ዛሬም የሰባት ጊዜ አሸናፊዎቹ ፈርኦኖቹ የጋናን ሜዳ በጥቁር ደመና በመሸበብ የክዋከብቱን ብርሃን እንዳይሸፍኑት ተሰግቷል ሲል ዘገባው ጨምሮ አስፍሯል፡፡
ግብጽ ከሞዛምቢክ ጋር ባደረገችው ግጥሚያ የበላይነትን ብትይዝም 2 ለ 2 በመለያየቷ ሦስት ነጥብ ማግኘት ግን ተስኗታል፤ ጉዳዩንም አሠልጣኝ ሩይ ቪቶሪያ እንዳሉት የትኩረት መጓደል ነው፡፡ “በዚያ ጨዋታ ትኩረት አጥተን ነበር፤ ነገር ግን አሁን ለማሸነፍ ተዘጋጅተናል” ማለታቸውን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል።
የአራት ጊዜ ሻምፒዮናዋ ጋና በኬፕ ቬርዴ 2 ለ 1 መሸነፏ ይታወሳል፡፡ ጥቁር ኮከቦቹ በሁሉም ውድድሮች ባደረጓቸው ያለፉት ስድስት ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ብቻ በማሸነፍ በቅርብ ጊዜ ደካማ የውድድር ዘመን አሳልፈዋል።
አሠልጣኝ ክሪስ ሂውተን “ጋና ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ ነጥብ ያስፈልጋታል፤ ስለዚህ ጠንክረን እንጫወታለን” ብለዋል፡፡ በመኾኑም ይህ ጨዋታ ለጥቋቁር ከዋክብቱ ወሳኝ ነው፡፡ ማሸነፍ በውድድሩ ለመቆየት የበለጠ ያግዛቸዋል፡፡
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!