ባሕር ዳር: የካቲት 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾቹ ብርቱካን ገብረ ክርስቶስ እና ረሂማ ዘርጋው ራሳቸውን ከብሔራዊ ቡድን ማግለላቸውን ማሳወቃቸው ይታወሳል። ይህን ተከትሎ ዛሬ በይፋ ሽኝት ተደርጎላቸዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን በወጥ ብቃት ለ20 ዓመታት ያገለገለችው ብርቱካን ገብረ ክርስቶስ ሀገሯን በሁለት አፍሪካ ዋንጫዎች ላይ ወክላለች።
በተጨማሪም በአራት የሴካፋ እና በሌሎች የአሕጉር እና ዓለም አቀፍ መድረኮች ተጫውታ አሳልፋለች። በአኹን ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እየተጫወተች የምትገኝው ብርቱካን ደደቢትን ጨምሮ በሌሎች ክለቦችም መጫወቷ የሚታወስ ነው።
በተመሳሳይ ብሔራዊ ቡድኑን ለ15 ዓመታት የወከለችው አጥቂዋ ረሂማ ዘርጋው በአንድ የአፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያን ወክላለች። ንግድ ባንክን ጨምሮ በሌሎች ክለቦች ተጫውታለች።
በአበበ ቢቂላ ስቴዲየም በተደረገላቸው የክብር ሽኝት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጅራ ለሁለቱም ተጫዋቾች የአንገት ሀብል እና የብሔራዊ ቡድኑን መለያ አበርክተውላቸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!