ባሕር ዳር: የካቲት 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሙሐመድ ሳላህ በዓለም ላይ ካሉ ምርጥ የእግር ኳስ ተጫዋቾች አንዱ በመኾን ዝናን ያተረፈ ግብጻዊ ኮከብ ነው። ሳላህ በሜዳ ላይ ባለው ፍጥነት፣ ቴክኒካዊ ችሎታ እና ግቦችን በማስቆጠር ብቃቱ ይታወቃል። ሳላህ በግብጽ በአንድ ትንሽ ከተማ ውስጥ ነው ያደገው። የእግር ኳስ ህልሙን ለመከታተል ጠንክሮ ሠርቷል።
በመጀመሪያ በአካባቢው ክለብ ውስጥ ተጫውቷል፤ ከዚያም ወደ ግብጽ ብሔራዊ ቡድን ተቀላቅሏል። እ.ኤ.አ. በ 2012 ሳላህ ወደ አውሮፓ ተዛውሮ ባሴል የተሰኘን ቡድን ተቀላቀለ። በስዊዘርላንድ ክለብ ውስጥ ባሳየው ጥሩ ብቃት ቼልሲ ቀጥሮት ወደ እንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ እንዲዛወር አደረገው።
በቼልሲ ብዙ የመጫወቻ ዕድል ያላገኘው ሳላህ በ2015 ሮማን ተቀላቅሏል። በጣሊያን ክለብ ውስጥ እራሱን አገኘ እና በፍጥነት የአንደኛ ቡድን ተጫዋች ኾነ። እ.ኤ.አ. በ2017 ሳላህ ሊቨርፑልን ተቀላቅሏል። በአንፊልድ የመጀመሪያ የውድድር ዘመኑ አስደናቂ ነበር እና የፕሪምየር ሊግ ወርቃማ ጫማን አሸነፈ።
ሳላህ ሊቨርፑልን በ2019 ቻምፒዮንስ ሊግ እና 2020 ፕሪምየር ሊግን ጨምሮ በርካታ ዋንጫዎችን እንዲያሸንፍ ረድቷል። ሳላህ ግብጽን በመወከል ወደ ዓለም ዋንጫም ተጉዟል። በ2018ቱ የዓለም ዋንጫ ላይ ግብጽን በመወከል ሁለት ግቦችን አስቆጥሯል። ሙሐመድ ሳላህ በሜዳ ላይ ባለው ችሎታው ብቻ ሳይኾን ከሜዳ ውጭ ባለው መልካም ባህሪውም ይታወቃል።
ለበጎ አድራጎት ሥራዎች ብዙ ገንዘብ ለግሷል። በተለይም በግብጽ በድኅነት ውስጥ ላሉ ወገኖቹ ይረዳል። ሙሐመድ ሳላህ የእግር ኳስ ተጫዋች ብቻ አይደለም። ለብዙ ወጣቶች አርዓያ መኾን የቻለ ነው። የእሱን ፈለግ በመከተል የእግር ኳስ ህልማቸውን እንዲያሳኩ አነሳስቷቸዋል። መሐመድ ሳላህ በግብጽ እና በዓለም ዙሪያ ለበርካታ በጎ አድራጎት ተግባራት ንቁ ተሳትፎ አድርጓል። ከእነዚህ መካከል በትውልድ መንደሩ ናግሪግ እና በሌሎች የግብጽ ከተሞች የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት እና ለማደስ የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል።
ሳላህ በግብጽ ውስጥ የሕፃናት የካንሰር ሆስፒታልን በመርዳትም አስተዋጽኦ እያደረገ ያለ ተጫዋች ነው። ሳላህ ለ57 ሺህ 357 የግብጽ ሕጻናትን ሕክምና እንዲያገኙ በመርዳትም ከብዙዎች ልብ ውስጥ እንዲገባም አስችሎታል። ሳላህ በግብጽ ላሉ አቅመ ደካሞች የምግብ እና አልባሳት ድጋፍ አድርጓል ሲል ብሪቲኒካ የተሰኘ ድረ ገጽ የተጫዋቹን የሕይዎት ታሪክ ባሰፈረበት አምድ አስነብቧል። “ማኅበራዊ አገልግሎትን ለራስህ ብለህ የምትሠራው ነው”ሲልም ተጨዋቹ ይናገራል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!