ባሕር ዳር 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “እኔም ለደሴ” በሚል መሪ መልዕክት በደቡብ ወሎ መዲና ደሴ ከተማ ሕዝባዊ ሩጫ ሊካሄድ ነው፡፡ የሕዝባዊ ሩጫው ዓላማ በ2017 የውድድር ዘመን በወንዶች ከፍተኛ ሊግ በምድብ ”ለ” ተደልድሎ ጨዋታዎችን እያደረገ ለሚገኘው ለደሴ ከተማ እግር ኳስ ቡድን ሁሉም ማኅበረሰብ ድጋፍ እንዲያደርግ እና ዕውቅና ለመስጠት ያለመ መኾኑን የደሴ ከተማ ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ እና የክለቡ የቦርድ ጸሐፊ ሰይድ አራጋው ለአሚኮ ተናግረዋል፡፡
ቡድኑ በከፍተኛ ሊጉ እየተወዳደረ የሚገኘው ከሜዳው ውጭ በመኾኑ አብዛኛው ማኅበረሰብ እና ደጋፊው ቡድኑ ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ መረጃ ስለሌለው በንቅናቄ ግንዛቤ ለመፍጠርም ታሳቢ መደረጉን አቶ ሰይድ ገልጸዋል፡፡ በውድድሩ ማንኛውም አቅሙ የፈቀደ የኅብረተሰብ ክፍል በሁለቱም ጾታዎች ተሳታፊ ይኾናሉ ነው የተባለው፡፡
ለውድድሩም የተለየ ”ቲ-ሸርት” መዘጋጀቱን የጠቆሙት አቶ ሰይድ ኅብረተሰቡም ቲ-ሸርቱን በመግዛት እና በውድድሩ ተሳታፊ በመኾን ክለቡን እያጠናከረ ለጤናው እንዲወዳደር ጠይቀዋል፡፡ ሕዝባዊ ሩጫው የካቲት 15/ 2017 ዓ.ም ከጠዋቱ 1:00 ሰዓት መነሻው እና መድረሻው ፒያሳ ይኾናል ብለዋል፡፡
ለውድድሩ ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ መምሪያ ኀላፊው ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡ በውድድሩ አሸናፊ ለሚኾኑት ሯጮች ሽልማት መዘጋጀቱንም አቶ ሰይድ ተናገረዋል፡፡ የደሴ ከተማ እግር ኳስ ክለብ በመጀመሪያው ዙር የከፍተኛ ሊግ ጨዋታ ምድቡን በአንደኛነት እየመራ እንደሚገኝም መምሪያ ኀላፊው ጠቁመዋል፡፡
የሁለተኛው ዙር የከፍተኛ ሊግ ምድብ ”ለ” ጨዋታዎች በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም በመደረግ ላይ ነው፡፡
ዘጋቢ፦ ሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን