ባሕር ዳር: ጥር 9/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ፋሲል ከነማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ዛሬ 12 ሰዓት በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ ከፍተኛ ፉክክር የሚደረግበት ይኾናል ተብሎ ይጠበቃል።
አፄዎቹ በ10 ጨዋታዎች አምስቱን አሸንፈው፣ በሦስቱ አቻ ተለያይተዋል፣ በሁለቱ ተሸንፈው እና በሰባት ንጹህ የግብ ክፍያ አምስተኛ ደረጃን ይዘዋል።ቅዱስ ጊዮርጊስም 10 ጨዋታዎችን አድርጎ በአምስቱ አሸንፎ፣ በሦሰቱ አቻ ተለያይቶ፣ በሁለቱ ተሸንፎ እና በዘጠኝ ንጹህ የግብ ክፍያ አራተኛ ኾኖ ተቀምጧል ሲል የኢትዮጵያ ፕሪሜየር ሊግ አክሲዮን ማኀበር ካምፖኒ በድረ ገጹ አስፍሯል።
ሁለት ተከታታይ ድል ያስመዘገቡት አፄዎቹ ይህንን ወሳኝ ጨዋታ ካሸነፉ ነጥባቸውን 21 አድርሰው ሁለት ደረጃዎችን ስለሚያሻሽሉ ጨዋታው ወሳኝነት አለው።
አፄዎቹ በጌታነህ ከበደ የቅጣት ምት ግብ ታግዘው ወልቂጤ ከተማን ባሸነፉበት ጨዋታ ላይ የደከመ የአማካይ ክፍል እንደነበራቸው ታይቷል። ይህንን ድክመታቸውንም በዛሬው ጨዋታ አርመው ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የአማካይ ክፍላቸው ላይ የአጨዋወት ለውጥ ካላደረጉ ጠንካራ የአማካይ ክፍል ያለውን ቅዱስ ጊዮርጊስ ስለሚገጥሙ ዋጋ ሊያስከፍላቸው ይችላል። ለአፄዎቹ ጌታነህ ከበደ ወደ ግብ አስቆጣሪነት መመለሱን ተከትሎ በፊት መስመር የነበረባቸውን የአጥቂ ክፍል ውስንነት የፈቱት አሠልጣኝ ውበቱ አባተ በመከላከሉ ረገድም ለተጋጣሚ ፈታኝ የኾነ የኋላ ክፍል ገንብተዋል።
ሁለቱ ቡድኖች የየራሳቸው የሚለዩበት ጥንካሬ ስላላቸው ጨዋታው ከፍተኛ ትኩረትን ስቧል። ሊጉ ከዕረፍት ከተመለሰ በኋላ ባደረጓቸው አራት ጨዋታዎች በአንዱ ድል፣ በሁለቱ አቻ እና በአንደኛው ደግሞ ሽንፈት አስተናግደዋል።
ውጤቱ እንደሚያመላክተው ፈረሠኞቹ በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ አይገኙም። ዛሬም ከሦስት ድል አልባ ጨዋታዎች መልስ ዳግም ሙሉ ሦስት ነጥብ አግኝተው ደረጃቸውን ለማሻሻል ወደ ሜዳ ይገባሉ።
ፈረሠኞቹ በሊጉ አስፈሪ የሚባል የማጥቃት ጥምረት ካላቸው ቡድኖች መካከል ይጠቀሳሉ። ቡድኑ ያስቆጠረው የግብ መጠንም የዚህ ምስክር ነው። ባለፉት ጥቂት ጨዋታዎች ግን የፊት መስመሩ ግብ ለማስቆጠር ሲቸገር ተስተውሏል።
ከዚህ ቀደም በክንፍ በሚደረግ ፈጣን ሽግግር የግብ ዕድሎች የሚፈጥር ቡድን ያስመለከቱን አሠልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ የተቀዛቀዘውን የፊት መስመር ዳግም ወደ ጥንካሬው የሚመልስ ውስን ጥገና ማድረግ ይኖርባቸዋል።
በዛሬው ዕለትም ተመሳሳይ ፈተና ሊገጥማቸው የሚችልበት ዕድል የሰፋ ስለኾነ አሠልጣኙ ለውጦችን ለማድረግ ይገደዳሉ ተብሎም ይገመታል ጨዋታውን ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ይመሩታል። ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ፋሲካ የኋላሸት እና ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ሙስጠፋ መኪ ረዳቶች ይኾናሉ ሲል ሶከር ኢትዮጵያ ዘግቧል።
ኢንተርናሽናል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ አራተኛ ዳኛ ኾነው ተመድበዋል። ከዚህ ጨዋታ አስቀድሞ ቀን 9 ሰዓት ላይ ሀምበርቾ ከሻሸመኔ ከተማ ይጫወታሉ።
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!