የፋሲል ከነማ ስደተኛው የሩጫ ውድድር በሁመራ መካሄድ ልዩ ትርጉም እንዳለው የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ገለጸ፡፡

0
110

ሁመራ: የካቲት 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የዞኑ ሁለተኛው የመላው ስፖርት ውድድር መክፈቻ በሁመራ ከተማ ተካሂዷል፡፡

በዚህ መርሐግብር የፋሲል ከነማ ስድስተኛው የሩጫ ውድድር ተካሂዷል፡፡ በዚህ ውድድር ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ገብረእግዚአብሔር ደሴ ፋሲል ከነማ ከክለብም በላይ ትርጉም ያለው መኾኑን ገልጸዋል። ፋሲል ከነማ የማንነታችን ሥሪት ነው ብለዋል።

ውድድሩ የቤተሰብ ነው ያሉት ኀላፊው ከነጻነት ማግስት የተገኘ ሌላ ድል መኾኑን አንስተዋል። ከነጻነት በፊት በነበሩት ጊዜያት የፋሲል ከነማ ማልያ ለብሳችኋል ተብለው በርካታ ወጣቶች ሕይወታቸውን ያጡ እንደነበር አስታውሰዋል። የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች እና መላው የስፖርቱ ቤተሰብ ለወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ አማራዊ ማንነት ፍሬ እንዲያፈራ ታግላችኋል ነው ያሉት።

የፋሲል ከነማ የቤተሰብ ሩጫ በዞኑ ሲካሄድ ለክለቡ ያለን ፍቅር እና ድጋፍ ለመግለጽ ድንቅ አጋጣሚ ፈጥሯል ብለዋል። መላው የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብም በማንነቱ እየኮራ፤ ፍላጎት እና ባሕሉን በነጻነት እየገለጸ ባለበት በዚህ ወቅት የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች ወደ በረሃዋ ገነት ወደ ሁመራ ከተማ በመምጣታቸው መደሰታቸውን ነው የተናገሩት፡፡

የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ወይዘሮ ብርሃን ነጋ የዞኑ ሁለተኛው መላው የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የስፖርት ውድድር በስምንት የተለያዩ የውድድር አይነቶች እንደሚካሄድ ገልጸዋል። ስድስተኛው የፋሲል ከነማ የገቢ ማሠባሠቢያ ሩጫ በዞኑ መደረጉ የሕዝቡን ስፖርታዊ ተሳትፎ እንደሚያሳድግም ኀላፊዋ ተናግረዋል።

ይህ የኾነው ዛሬ የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ነጻነቱን በማግኘቱ ነው ያሉት ኀላፊዋ ነጻነትን በማስቀጠል ሕዝቡ ፍላጎቱን እንዲህ በአደባባይ መተንፈስ እንዲችል ስለተደረገ ኩራት እንደሚሰማቸው ገልጸዋል።

ሩጫው ትልቅ መነቃቃት እንደፈጠረ አሚኮ ያነጋገራቸው የሩጫው ተሳታፊዎች ተናግረዋል። ከለውጥ በፊት የፋሲልን ማልያ መልበስ ዋጋ ያስከፍል ነበርም ብለዋል። ዛሬ ግን በነጻነት የፈለጉትን በማድረጋቸው እንደተደሰቱም ነው ያብራሩት፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here