የመላው ዋግ ኽምራ ዘመናዊ ስፖርት ውድድር ለታዳጊዎች እድል የፈጠረ ነው።

0
188

ሰቆጣ: የካቲት 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 9ኛው የመላው ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዘመናዊ ስፖርት ውድድር በጋዝጊብላ ወረዳ እየተካሄደ ነው። በውድድሩ ተተኪ ስፖርተኞች ወረዳቸውን በመወከል ተስፍ ሰጭ ችሎታቸውን እያሳዩ ይገኛሉ።

የድሃና ወረዳ የፊት መስመር የእግር ኳስ ተጫዋቹ ዳዊት እንግዳ በኳስ ችሎታው የውድድሩ ድምቀት ኾኗል።የ14 ዓመቱ ታዳጊ በውድድሩ ብቃቱን እያሳየ ነው።

የወደፊት ህልሙ በኢትዮጵያ ፕሪምዬር ሊግ መጫወት እንደኾነ የሚናገረው ተስፈኛው አጥቂ ዳዊት ይህ ውድድር የተለየ ችሎታውን ለማሳየት ጥሩ አጋጣሚ እንደኾነለት ተናግሯል።

የጻግቭጂ ወረዳው አጥቂ ኪዳኔ ንጉሤ ውድድሩ ለተተኪዎች ምቹ ዕድልን የፈጠረ መኾኑን ገልጿል።

ወረዳውን ሲወክል ለመጀመሪያ ጊዜ እንደኾነም ተናግሯል። የዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ የስፖርት እና ውድድር ቡድን መሪ አበራ ቢምረው የመላው ዋግ ኽምራ የዘመናዊ ስፖርት ውድድር ከሰባቱ ወረዳዎች እና ሦስት ከተማ አሥተዳደሮች ከታዳጊ ፕሮጀክቶች የተመለመሉ ከ90 በላይ ስፖርተኞችን ማሳተፉን ገልጸዋል።

የውድድሩ ዓላማ ታዳጊዎችን ልምድ ካላቸው ተጫዋቾች ጋር በማዋሃድ ዋግ ኽምራን በመወከል በደሴ ከተማ ለሚካሄደው የመላው አማራ ክልል ዘመናዊ ስፖርት ውድድር ውጤታማ መኾን ነው ብለዋል። ተተኪ ስፖርተኞችም ችሎታቸውን በማሳየት ራሣቸውን ለትልቅ ደረጃ የሚያጩበት ዕድል ከእጃቸው እንደኾነ አውቀው በጥሩ ብቃት እንዲጫወቱ አሳስበዋል።

ዘጋቢ: ደጀን ታምሩ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here