አውቆ አጥፊነት ወይስ?

0
194

ባሕር ዳር: የካቲት 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በዓለም ላይ የምንኖር ሰዎች ሁሉ የምንተዳደርበት ሕግ ባይኖር ኖሮ ምን እንኾን ነበር? ብዬ ሳስብ በጣም እገረማለሁ፡፡ ሕግም ኾነ መንግሥት የሌላቸውን ሀገራት ዜጎች የአኗኗር ኹኔታ ስመለከት መተዳደሪያ ደንብ ወይም ሕግ ለሰዎች ምን ያኽል ዋጋ እንዳለውም እገነዘባለሁ፡፡

የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ስለ ሕግ ጠቀሜታ ማብራራት አይደለም፤ ይልቁንም በየትኛውም የሙያ መስክ ላይ ሕግ የማይከበር ከኾነ፣ ብዙ ነገሮች እንደሚበላሹ እና ሙያውም ርካሽ እንደሚኾን መታዘቤን ለመግለጽ ፈልጌ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ፕርምየር ሊግ እና ከታች ባሉ የሊግ እርከኖች የምናያቸው የጨዋታ ሕጎችን ያለማስከበር ጉዳይ ለእግር ኳሳችን ውድቀት አንደኛው ማሳያ ነው ብዬ ባስብ የተሳሳትኩኝ አይመስለኝም፡፡

በኢትዮጵያ ፕርምየር ሊግ እና ከታች ባሉት የሊግ እርከኖች ጭምር ዳኞችን መሳደብ፣ ማንጓጠጥ፣ ማመናጨቅ እና አንዳንዴም መማታት የተለመደ ኾኗል፡፡ ተጨዋቾች ዳኞችን የሚወቅሱበት ወይም በዳኞች የመዳኘት ብቃት ላይ ጥያቄ የሚያነሱባቸው በርካታ ክስተቶች እንደሚፈጠሩ እሙን ነው፡፡ ዳኞቹ ኾን ብለው እና ከመዳኘት ብቃት ማነስ የሚሰጧቸውን ውሳኔዎች ለእግር ኳሱ አሥተዳዳሪዎች ከማሳወቅ አልፎ በዳኞች ላይ ርምጃ ለመውሰድ መሞከር ግን በየትኛውም መስፈሪያ ልክ ሊኾን አይችልም፡፡

በኢትዮጵያ ፕርምየር ሊግ ውስጥ የምናያቸው የተሳሳቱ የዳኝነት ውሳኔዎች እንኳንስ ለተጨዋቾች ይቅርና ለኛ ለተመልካቾችም የሚያበሳጨን ጊዜ በርካታ ነው፡፡ ግን ደግሞ ዳኞቹ ተሳሳቱ ብሎ በመክበብ የደቦ ርምጃ ለመውሰድ መጣር የተጨዋቾቹን ስህተት ከዳኞቹም በላይ ያደርገዋል፡፡

የእግር ኳስ ተጨዋቾች የዓለም እግር ኳስ አሥተዳዳሪው (ፊፋ) በአዲስ የሚያወጣቸውን ሕጎች እና ከነባሮቹም የሚያሻሽላቸውን ሕጎች ከማንም በላይ ጠንቅቀው የማወቅ ግዴታ አለባቸው፡፡ ተጨዋቾቹ ሕጎቹን ሲተላለፉ ሊጣልባቸው የሚችለውን ቅጣትም አብረው የማወቅ ግዴታ አለባቸው፡፡ ለምን? ከተባለ ደግሞ እግር ኳስ ለእነሱ እንጀራ የሚጎርሱበት ሙያቸው ስለኾነ የሚል ምላሽ ይኖረናል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ እግር ኳስ በጣም የሚወደድ እና ብዙ ተመልካቾች እንዲሁም ደጋፊዎች ያሉት ስፖርት እንደኾነ ይታወቃል፡፡ በዚህ የስፖርት ዘርፍ ሀገራችን ምንም እንኳን ውጤታማ ናት ማለት ባንችልም በዘርፉ ላይ የሚፈሰው መዋዕለ ነዋይ ግን ቀላል የሚባል አይደለም፡፡

ለአንድ ተጨዋች በወር እስከ 500 ሺህ ብር እና ከዚያም በላይ የሚከፈልበት እግር ኳሳችን ብሔራዊ ቡድናችንን እንደ ቅጽል ስሙ (ዋሊያ) ከሀገራችን የማያስወጣው ከኾነ ፋይዳው አንሶ መታየቱ አይቀርም፡፡

በኢትዮጵያ ፕርምየር ሊግ ውስጥ የምናያቸው አንዳንድ ተጨዋቾች እንኳንስ በወር 500 ሺህ ብር ሊከፈላቸው ይቅርና እኛ እነሱን ለ90 ደቂቃዎች ያኽል ሥራ ፈትተን ስላየናቸው ሊከፍሉን የሚገባን ነን፡፡ የዚህ ዓይነት ተጨዋቾች በሜዳ ውስጥ ከተቃራኒ ተጨዋቾች ጋር መጣላት እና የዳኞችን ውሳኔ ደጋግሞ መቃወምን ለሚከፈላቸው ዳጎስ ያለ ደመወዝ ሲሉ የሚፈጽሙት ይመስላሉ፡፡

በኢትዮጵያ ፕርምየር ሊግም ኾነ ከታች ባሉት የሊግ እርከኖች የሚጫወቱ ተጨዋቾች ለዳኞች ብቻ ሳይኾን ለተመልካቾች ያላቸው ንቀት በእጅጉ የሚያሳዝን ነው፡፡ እግር ኳስን ተጫውተው ያሳለፉ ወይም እግር ኳስን በመመልከት የሚዝናኑ በርካታ ደጋፊዎች የእግር ኳስ ሕጎችን ከተጨዋቾች ባልተናነሰ መልኩ እንደሚያውቁ ግምት ውስጥ መግባት ይኖርበታል፡፡ የስፖርት ጋዜጠኞች ምልከታም ወደ ጎን ሊተው አይገባውም፡፡

በኛ ሀገር ሜዳዎች ላይ የምናየው የሰዓት አገዳደል የምር የሚያሳዝን ነው፡፡ አንድ ግብ ጠባቂ የሱ ቡድን በውጤት እየመራ ከኾነ ኳሷ ወደሱ በመጣች ቁጥር ኳሷን አቅፎ በመተኛት የሚያባክነው ደቂቃ በየትኛውም የውጭ ሀገር ሊጎች ላይ አትመለከቱትም፡፡ ተጨዋቾችም ቢኾኑ ምንም አይነት ግጭት ሳያጋጥማቸው ሜዳ ላይ ወድቀው ሲንከባለሉ፣ ሐኪም ገብቶ እርዳታ ሲሰጣቸው ያለመነሳት፣ የተቃራኒ ተጨዋቾች ሊያነሷቸው ሲሞክሩ ወደ ጠብ መግባት እና ሌሎችም አጸያፊ ድርጊቶቻቸው በሌሎች ሊጎች የሚታዩ አይደሉም፡፡

ዳኞችን ከብቦ ውሳኔ ለማስቀየር የሚደረገው ጥረት በአውሮፓ ውስጥ በሚገኙ ትላልቅ ክለቦች ተጨዋቾችም የሚፈጸም ቢኾንም እንደኛ ሀገር ተጨዋቾች ዳኞችን እየጎነተሉ ውሳኔ ለማስቀየር መሞከር ግን ለሌላ የከፋ ቅጣት የሚዳርግ ክስተት ነው፡፡ በኛ ሀገር ዳኞችን በኀይለ ቃል እየተናገሩ እና ልብሳቸውን እየጎተቱ ውሳኔዎችን ለማስቀየር መሞከር በሕጉ ላይ የተፈቀደ ሁሉ ይመስላል፡፡ የብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾቻችንም ቢኾኑ በፕርምየር ሊጉ የለመዱትን የዳኞችን ውሳኔ ያለማክበር ጉዳይ በኢንተርናሽናል ጨዋታዎች ላይም ሲደግሙት ታዝበናል፡፡

በውጭ ሀገር በምናያቸው ትላልቅ ጨዋታዎች ላይ ዳኞች ፍጹም የኾነ ስህተት ይሠራሉ፤ ክለቦችም በዳኞች የተሳሳቱ ውሳኔዎች ውጤት ያጣሉ፤ ያም ቢኾን ግን ዳኞቹ ሜዳ ውስጥ በተጨዋቾች አንዳችም ጉንተላ አይደርስባቸውም፡፡

በእርግጥ የውጭ ጨዋታዎች በቪዲዮ ረዳት ዳኝነት (ቫር) ጭምር የሚታገዙ በመኾናቸው የዳኞችን ስህተት ለማረም ዕድሉ ይኖራል፡፡ ዳኞች ጨዋታውን በቫር ሳያዩ በሚወስኗቸው የተሳሳቱ ውሳኔዎችም ግን በተጨዋቾች ሲሰደቡ እና ሲመናጨቁ አናያቸውም፡፡ ይህንን በስፋት የምናየው በኛው ሀገር ጨዋታዎች ነው፡፡

በኛ ሀገር በዳኞች ላይ ለሚደርሱት ማዋከቦች የአሠልጣኞችም ሚና የላቀ ነው፡፡ አሠልጣኞቹ ከሜዳ ውጭ ኾነው የሚያሳዩዋቸው ያልተገቡ እንቅስቃሴዎች ተጨዋቾች በዳኛው ላይ እንዲያምጹ ቤንዚል ኾነው የሚያገለግሉ ናቸው፡፡

የአሠልጣኞቹ ሕግን ያልተከተለ የፍትሕ ጥያቄ ተመልካቾች በዳኛው ላይ ተቃውሞ እና ስድብ እንዲያሰሙም በር ሲከፍት አስተውለናል፡፡ ይህ ሁሉ የሚፈጸመው ደግሞ ሕጉን ካለማወቅ ሳይኾን በሜዳ ላይ ለጠፋ ውጤት ዳኞችን ሰበብ ለማድረግ ከመፈለግ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ፕርሚየር ሊግ በዲኤስቲ ሲተላለፍ ብዙ ተተኪ ተጨዋቾች ጨዋታውን ይከታተሉታል ብሎ ማሰብ በጎ ነው፡፡ እነዚህ እግር ኳስን የነገ ሙያቸው ለማድረግ የሚጥሩ ታዳጊዎች በየጨዋታዎቹ ከተጨዋቾች የሚያዩት የዲሲፕሊን ግድፈት እንደ አንድ ጥሩ ሙያ መማር አይኖርባቸውም፡፡

ታዳጊዎቹ አርዓያ ያደረጓቸው ተጨዋቾች በሜዳ ላይ የሚያሳዩትን ያልተገባ ባሕሪ እንዳይኮርጁም መጠንቀቅ ይገባል፡፡

ውጤት አልባ በኾነው እግር ኳሳችን ላይ ሥነ ምግባር የሌላቸው ተጨዋቾች በዝተው ማየታችን በነገው የእግር ኳስ ውጤታችንም ላይ ተስፋ እንዳናደርግ ምክንያት ይኾናል፡፡ ከጥቅም ጋር የተያያዙ ውሳኔዎቻቸው አደብ ካልገዙም የእግር ኳሳችን ትንሳኤ ሩቅ ይኾናል፡፡

ዘጋቢ፡- እሱባለው ይርጋ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here