ያ ትውልድ !

0
179

ባሕር ዳር: ጥር 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) እግር ኳስ ይወደዳልም ይዘወተራልም። በልኩ አለማደጉ እና ውጤት አለማገኘቱ ደግሞ ብዙዎችን ያበሳጫል። እግር ኳስ በኢትዮጵያውያን በእጅጉ ተወዳጅ ስፖርት ለመኾኑ በየሰፈሩ ከጨርቅ እስከ ላስቲክ ኳስ የሚያንከባልለውን ሰው ብዛት ማየት በቂ ነው።
የአውሮፖ ከለቦችን ጨዋታ ለመመልከት በየቦታው የሚሠባሠበውን እግር ኳስ አፍቃሪንም መጨመር ይቻላል።

አሳዛኙ ነገር ግን እግር ኳስ እንዲህ በሚወደድበት ምድር ብሔራዊ ቡድኑ እና ክለቦች ተወዳዳሪ አለመኾናቸው ነው። የአፍሪካ አግር ኳስ ባለውለታዋ ኢትዮጵያ ማንም ከኋላ ተነስቶ የሚቀድማት፣ የግብ ማወራረጃ መኾኗ ሰነበተ። ክፋቱ ደግሞ የእግር ኳሱ ሕመም ተለይቶ መድኃኒት አለመገኘቱ ሲኾን ይህም ነገ ላይ እንኳ ተስፋ እንዳይኖር አድርጓል።

ይህ የዛሬ መራራ ሀቅ ቢኾንም ትናንት ግን ኢትዮጵያ በእግር ኳሱ የተሻለ ስም ነበራት። በተለይ የአፍሪካ ዋንጫን በመመስረት ትልቅ ባለውለታ ናት። ከመመስረት በተጨማሪም በመጀመሪያዎቹ ውድድሮች በመሳተፍ እና ውድድሩን በማዘጋጀትም ጭምር የእግር ኳስ ሀገር ናት። ሦስተኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ማሸነፏ ደግሞ በመሰረተችው ውድድር የምትናገረው ታሪክ እንዲኖራት አድርጓል።

ጊዜው 1954 ዓ.ም ነው። ሦስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ በአዲስ አበባ ተደግሷል። አንደኛው እና ሁለተኛው የአፍሪካ ዋንጫ በሱዳን እና ግብጽ ተከናውኖ ግብጽ አሸናፊ ኾናለች። ሦስተኛው ዋንጫ በአዲስ አበባ በያኔው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ስታድየም ሲካሄድ ኢትዮጵያ አዘጋጅ በመኾኗ፣ ግብጽ ደግሞ ያለፈውን ዋንጫ ባለድል በመኾኗ ማጣሪያ ሳያደርጉ በቀጥታ አለፉ።

ቱኒዚያ፣ ሞሮኮ፣ ጋና፣ ናይጀሪያ፣ ኬንያ፣ ሱዳን እና ኡጋንዳ ማጣሪያ አደረጉ። ቱኒዚያ እና ኡጋንዳ ማጣሪያውን አልፈው ኢትዮጵያ እና ግብጽን ተቀላቀሉ። አራቱ ቡድኖች በዕጣ ኢትዮጵያ ከቱኒዚያ እና ግብጽ ከኡጋንዳ ተመደቡ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዝግጅቱን ቀደም ብሎ ጀምሯል። በወዳጅነት ጨዋታ ኬንያን 4ለ3 እና 6ለ1 በማሸነፍ ጥሩ ወኔ ላይ ነው።

ጥር6/1954 ዓ.ም ለዋንጫ ለመድረስ ኢትዮጵያ ከቱኒዚያ ተጫወቱ። የደጋፊው ስሜት የተለየ ነበር። ምክንያቱም ባለፉት ዋንጫዎች ብሔራዊ ቡድኑ ከመሳተፍ ውጭ ድል አላስመዘገበም። አሁን ይሄ ታሪክ መቀየር አለበትና ነው። በጨዋታው ኢትዮጵያ 4ለ2 አሸነፈች። በዚያ በኩል ደግሞ ግብጽ እና ኡጋንዳ ተጫወቱ እና ግብጽ አሸነፈች። ለዋንጫ ኢትዮጵያ ከግብጽ ተፋጠጡ።

አዲስ አበባ ሃሳቧ ለሁለት ተከፈለ። አንዱ የግብጽ ማለፍን እንደመጥፎ ዕድል ቆጠረ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ግብጽ በአንደኛው እና ሁለተኛው የአፍሪካ ዋንጫ በኢትዮጵያ ላይ ለወሰደችው የበላይነት ጥሩ የበቀል ጊዜ ነው ተባለ። ጥር 13/1954 ዓ.ም ብዙ የተወራለት፣ ብዙ የተመከረበት እና ብዙዎች እንቅልፍ ያጡለት የዋንጫ ጨዋታ ኢትዮጵያ ከግብጽ በቀዳማዊ ኅይለ ሥላሴ ስታድየም ተካሄደ።

ስታድየም ውስጥ ግርማዊ ቀዳማዊ ኅይለ ሥላሴን ጨምሮ ሜዳው የጠጠር መጣያ የለውም። ጨዋታው ተጀመረ። ሜዳው ውስጥ እልህ እና ፍርሃት ይታያል። የግብጽ ብሔራዊ ቡድን በአንደኛው እና ሁለተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ሱዳን እና ኢትዮጵያን በሰፊ ግብ እያሸነፈ የዋንጫ ባለቤት ኾኗል። ይሄ ለብዙዎች ፍርሃት ፈጥሯል። በሌላ በኩል ደግሞ የማይነካ የመሰለውን የግብጽ ቡድን አንገት ለማስደፋት ወኔ የፈነቀለው ብዙ ነው።

ጨዋታው ተጀምሮ ብዙ ደቂቃ ሳይጓዝ ግብጾች አገቡ፣ የሞቀው ስታድየም ድባብ ጸጥ አለ። የመጀመሪያው የጨዋታ ጊዜ በዚሁ ውጤት ተጠናቀቀ። ተጫዋቾች ወደ መልበሻ ክፍል ሲገቡ ተመልካቹ እንዲህ አለ” መሸነፍ አይቻልም፤ አዎ በግብጽ መሸነፍ ያመናል”።

ውጥረቱ ጣሪያ የነካው ሁለተኛ የጨዋታ ጊዜ ተጀመረ ኢትዮጵያ በተክሌ(ወዲ ቀጭን) አማካኝነት አቻ ኾነች። አዲስ አበባ በአንድ እግሯ ቀመች። ግን የግብ ቀበኛው መሐመድ በዳዊ ወዲያው ግብጽን መሪ አደረገ። ቢኾንም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጭኖ መጫወት ጀመረ።

ደቂቃው እየነጎደ ነው ስታድየሙ ለግብጾች እሳት፣ ለኢትዮጵያውያን ብርታት ኾኖ ቀጠለ። በግብጽ መሸነፍ ያመናል በሜዳው አራቱም አቅጣጫ ክፍ ብሎ ይሠማል።

በመጨረሻ ሉቻኖ ቫሳሎ ኢትዮጵያን ከጉድ ታደገ። ጨዋታው ከመጠናቀቁ በፊት ግብ አስቆጠረ። በደስታ የተቃቀፈ፣ ያለቀሰ፣ ይይዘው ይጨብጠውን ያጣውን ቤት ይቁጠረው።

ጨዋታው በጭማሪ ሰዓት ሲቀጥል ግብጾች ጉልበታቸው ራደ። መንግሥቱ ወርቁ፣ ቫሳሎ እና ኢታሎ ቫሳሎ ለግብጽ ተከላካዮች ፈተና ኾኑ።

ኢታሎ ሦስተኛውን፣ መንግሥቱ ደግሞ አራተኛውን ግብ አከታትለው አስቆጠሩ። ጨዋታው 4ለ2 ተጠናቀቀ። አምበሉ ሉቺያኖ ዋንጫውን ከቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ እጅ ተቀበለ።

አያ ሆሆሆ…ማታ ነው ድሌ ከስታድየም አልፎ ምሽቱን ሙሉ በአዲስ አበባ ሲደለቅ ማምሸቱን የቆዩ የጋዜጣ ጹሑፎች እና በተለያየ ጊዜ የተላለፉ የራዲዮ ዝግጅቶች እማኝ ናቸው።

በአፍሪካ ዋንጫም ብቸኛው ድል ይህ የእነ መንግስቱ ወርቁ እና የቫሳሎዎች ገድል ነው።

ይህ ድል ከተገኘ ዛሬ 63 ዓመት ሞላው። ክብር ለባለታሪኮቹ፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here