አሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ኾነው ተሾሙ።

0
179

ባሕር ዳር: ጥር 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድን የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ አድርጎ ሾሟል።

አሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድ ከዚህ ቀደም የሐዋሳ ከተማ ሴቶች ቡድን እና ባለፉት ሦሰት ዓመታት ደግሞ የአርባምንጭ ከተማ ሴቶች ቡድን ዋና አሰልጣኝ በመኾን ሲሠሩ ቆይተዋል።

ባለፈው ዓመት በጋና አክራ በተካሄደው የአፍሪካ ጨዋታዎች ላይም የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድንን አሰልጥነዋል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ትናንት ባደረገው ስብሰባ አሰልጣኝ ዮሴፍ የብሔራዊ ቡድኑን ኃላፊነት እንዲረከቡ ውሳኔ ማሳለፉ ነው የተመላከተው። አሰልጣኙ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድንን ለቀጣይ ሁለት ዓመታት ለማሰልጠን ተስማምተዋል።

ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው አሰልጣኝ ዮሴፍ ከአንድ ወር በኋላ በ2026 የሴቶች አፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ የመጀመርያ ዙር ዩጋንዳን የሚገጥመውን ቡድን በማዘጋጀት የብሔራዊ ቡድን ሥራቸውን ይጀምራሉ።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለአሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድ መልካም የሥራ ጊዜ ተመኝቶላቸዋል። የአሰልጣኙን ቅጥር እና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ወደፊት በሚገለፅ ቀን ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጥም ተመላክቷል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here