ባሕር ዳር: ጥር 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የእንግሊዝ ፕሪምየርሊግ የ21ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ጀምረው ይካሄዳሉ። ዛሬ ከሚደረጉ ጨዋታዎች መካከል የሊጉ መሪ ሊቨርፑል በስድስት ነጥብ አንሶ ሦስተኛ ላይ ከተቀመጠው ኖቲንግሃም ፎረስት ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
ሊቨርፑል አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በ46 ነጥብ ሰንጠረዡን እየመራ ነው። በ40 ነጥብ በአርሰናል በግብ ክፍያ ተበልጦ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የተገኘው ደግሞ ኖቲንግሃም ፎረስት ነው። ዘንድሮ የሊጉ ክስተት ኾኖ የቀረበው ኖቲንግሃም ከሚታወቅበት በሊጉ የመሰንበት ትግል ወጥቶ ለዋንጫ የሚያፎካክረው ደረጃ ላይ ተገኝቷል።
ዛሬ ሊቨርፑልን መርታት ከቻለም ከመሪው ጋር የሚኖረው የነጥብ ልዩነት ሦስት ብቻ ይኾናል። ኖቲንግሃም ጨዋታውን በሜዳው የሚያከናውን በመኾኑ ቀዩቹን ሊፈትኑ እንደሚችሉ ተገምቷል። በሌሎች ጨዋታዎች ብሬንትፎርድ ከማንቸስተር ሲቲ፣ ቼልሲ ከበርንማውዝ እና ዌስትሃም ከፉልሃም ይጫወታሉ።
ከነበረበት መውረድ ለመመለስ ጥረት እያደረገ ያለው ሲቲ በቅርብ ጨዋታዎች ያገኘውን አሸናፊነት ለማስቀጠል በሜዳው ጥንካሬው ከሚጎላው ብሬንት ፎርድ ከባድ ፈተና ያገኘዋል። በተቃራኒው በቅርብ ጨዋታዎች ውጤት የራቀው ቼልሲ ከበርንማውዝ ጋር ይጫወታል።
በውጤት ማጣት ምክንያት አሠልጣኝ የቀየረው ዌስትሃም ደግሞ በለንደን ደርቢ ከጠንካራው ፉልሃም የሚያደርጉት ጨዋታዎችም ተጠባቂ ነው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!