ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 12ኛ ሳምንት ዛሬ ሲቀጥል አዳማ ላይ ሁለት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ። በዛሬው ጨዋታ ባሕር ዳር ከተማን ከደሬዳዋ ከተማ 9 ሰዓት የሚያገናኘው ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
18 ነጥብ በመሠብሠብ በደረጃ ሰንጠረዡ 3ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ባሕርዳር ከተማ በ16 ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውን ድሬዳዋ ከተማን ነው የሚገጥመው። የአሠልጣኝ አብርሃም መብራቱ ቡድን አሁን ያለበት ወቅታዊ አቋም ጥሩ ነው ባይባልም የከፋ የሚባል ግን አይደለም።
ቡድኑ ባለፉት ጊዜያት ከአደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች ውስጥ ሦስቱን ነጥብ ሲጋራ አንድ ጊዜ ተሸንፎ አንድ ጊዜ ደግሞ አሸንፏል።ቡድኑ ከዚህ በፊት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር 0 ለ 0፤ ከመቀሌ70 እንደርታ ጋር 1 ለ 1 እና ከወላይታ ዲቻ ጋር 0 ለ 0 በመለያየት ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል።
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 3 ለ 0 የተሸነፈው ባሕር ዳር ከተማ ሽሬንዳስላሴን 2 ለ 0 ማሸነፍ ችሏል። በ11 ጨዋታዎች 11 ጎል ማግባት የቻሉት ባሕር ዳር ከተማዎች በ12ኛ ሳምንት ጨዋታ ተጋጣሚያቸውን በመርታት ሦስት ነጥብ ይዘው ከመውጣት ባለፈ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታ እያለው በ21 ነጥብ በደረጃ ሠንጠረዡ አናት ላይ የሚገኘውን መቻል በቅርብ ርቀት ለመከተል እንዲችሉ ታሳቢ አድርገው ወደ ሜዳ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የዋዛ እንዳልኾነ ወቅታዊ አቋሙ የሚያሳየው ድሬዳዋ ከተማም ጨዋታውን ለማሸነፍ ወደ ሜዳ ይገባል። ቡድኑ ከዚህ በፊት ካደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች ውስጥ አንድ ጊዜ ሲሸነፍ ሁለት ጊዜ ደግሞ አቻ እና ሁለት ጊዜ ነጥብ ተጋርቶ መውጣት ችሏል።
ቡድኑ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ያለምንም ግብ ተለያይቷል። በሲዳማ ቡና 3 ለ 1 የተረታው ድሬዳዋ ከተማ ሀዋሳ ከተማን እና ሀድያ ሆሳዕናን 1ለ0 በማሸነፍ ያለው ጥሩ ወቅታዊ ብቃት ለባሕር ዳር ከተማ ፈታኝ እንደሚኾን ይጠበቃል።
ቡድኑ በ10 ጨዋታዎች 14 ጎል በማስቆጠር ከባሕር ዳር ከተማ የተሻለ ነው። ሁለቱ ቡድኖች የተሻለ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ የሚጠበቅ ይሁን እንጅ የሚያደርጉት የ90 ደቂቃ ጨዋታ መልስ ይሰጣል።
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 12ኛ ሳምንት ጨዋታ ሲቀጥል 12 ሰዓት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!