ባሕር ዳር: ጥር 07/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በውጤት እጦት ውስጥ የሚገኘው ሮማ አሠልጣኙን አሰናብቷል።
በፖርቶ፣ ቼልሲ፣ ኢንተርሚላን እና ሪያል ማድሪድ በአሠልጣኝነት ትልቅ ክብር ያስገኘላቸውን ሥራ የሠሩት ሞሪንሆ በዚህ የውድድር ዘመን በሮማ ቤት መንገዳቸው ቀና አልኾነም።
በቅርቡ በጣሊያን ሴሪኤ ካከናወኗቸው ስድስት ጨዋታዎች ያሸነፉት አንዱን ብቻ ነው። ሮማ አሁን ላይ ከሴሪኤው መሪ ኢንተርሚላን በ22 ነጥብ ያንሳል። በኮፓ ኢታሊያ በላዚዮ ተሸንፈው ከውድድሩ መውጣታቸውም ለሞሪኒሆ በሮማ ቤት መገፋት እንደ አሁናዊ ምክንያት ተቆጥሯል።
ስካይ ስፖርት እንዳስነበበው ሞሪንሆ በሁለት ዓመት ተኩል የሮማ ቆይታቸው ክለቡን ለኮንፍረንስ ዋንጫ አብቅተውታል። ለክለቡ ከረዥም ዓመታት ወዲህ የተገኘ ድል በመኾኑም ልዩውን ሰው የሮማ ደጋፊዎች አንቱ ብለው አክብረዋቸዋል።
ባለፈው ዓመት በዩሮፓ ሊግ ለፍጻሜ መድረሳቸውም ፖርቱጋላዊውን አሠልጣኝ አስወድሷቸው ነበር። ነገር ግን በዚህ የውድድር ዘመን የክለቡ ውጤት በተጠበቀው ልክ ባለመኾኑ አሠልጣኙ ለመሰናበታቸው ምክንያት ኾኗል።
የሮማ ክለብ ሞሪንሆ ለሮማ በሰጡት አገልግሎት ክብር ሰጥቶ አመሥግኗቸዋል። ጆዜ ሞሪንሆ ቀጣይ ሥራቸው በሳኡዲ ፕሮ ሊግ ሊኾን እንደሚችልም ቢቢሲ አስነብቧል።
በአስማማው አማረ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!