ባሕር ዳር: ጥር 7/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በሊጉ የ11ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ሲቀጥል ቀን 9 ሰዓት ላይ ወላይታ ድቻ ከሀዋሳ ከተማ፤ ምሸት 12 ሰዓት ወልቂጤ ከተማ ከአዳማ ከተማ ይጫወታሉ፡፡
የጦና ንቦቹ ወላይታ ድቻዎች በ10 ጨዋታ አምስቱን አሸንፈው፣ በሁለቱ አቻ ወጥተው እና በሦስቱ ተሸንፈው በአንድ ንጹህ የግብ ክፍያ 17 ነጥብ በመሠብሠብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
ቡድኑ በመጨረሻው የቅርብ ጊዜ ጨዋታ በሊጉ መሪ ንግድ ባንክ ላይ ወሳኝ ድል ተቀዳጅቷል፡፡ ሌላው የቡድኑ ጥንካሬ በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ ካሉ ሦስት ቡድኖች ጋር ባደረጋቸው ጨዋታዎች ሁለቱን ማሸነፍ መቻሉ ነው፡፡ ይህም የቡድኑን መሻሻል ያሳየ ነው ተብሏል።
የጦና ንቦቹ ከዚህ ቀደም የግብ ዕድሎችን በመጠቀም ረገድ ክፍተቶች ነበሩባቸው ፤ አሁን ግን በማጥቃት የአጨዋወት ስልት ላይ መጠነኛ መሻሻል አሳይተዋል። ወላይታ ድቻ በወቅታዊ አቋሙ ከቀጠለም ሀዋሳን ሊፈትነው ይችላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በጉዳት ምክንያት ባዬ ገዛኸኝ፣ መልካሙ ቦጋለ እና አብነት ደምሴ ከዛሬው ጨዋታ ውጪ መኾናቸው ተረጋግጧል። ወቅታዊ አቋሙ እየዋዠቀ የሚገኘው ሃይቆቹ ሀዋሳ ከተማዎች በ10 ጨዋታ ሁለቱን አሸንፈው፣ በሦስቱ አቻ ወጥተው እና በአምስቱ ተሸንፈው በሰባት የግብ ክፍያ 9 ነጥብ በመያዝ ከወራጅ ቀጣናው በአንድ ነጥብ ብቻ ከፍ ብለው በ13ኛ ደረጃ ላይ መቀመጣቸውን የኢትዮጵያ ፕሪሜየር ሊግ አክሲዮን ካምፓኒ በድረ ገጹ አስታውቋል፡፡
አሠልጣኝ ዘረስናይ ሙሉ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች በቀላሉ ግቦችን አስተናግደዋል፡፡ የተከላካይ መስመራቸው ላይም ሁነኛ ለውጥ ማድረግ ግድ ይላቸዋል። በተጨማሪም የፊት መስመሩ ላይ በብልጠት በመጫዎት ግብ የሚያስቆጥሩበትን ዘዴ መቀየስ ይኖርባቸዋል፡፡
በሀዋሳ ከተማ በኩል ሙጂብ ቃሲም በእግድ ምክንያት አይሰለፍም፡፡ ለሀይቆቹ መልካሙ ዜና በቅጣት ላይ የነበሩት መድሓኔ ብርሃኔ እና ኢዮብ ዓለማየሁም ከቅጣት ተመልሰዋል።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 18 ጊዜ ተገናኝተዋል፡፡ ወላይታ ድቻ ሰባት ጊዜ አሸንፏል፡፡ ሀዋሳ ደግሞ አምስት ጊዜ ድል አድርጓል። በስድስት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
ምሽት12 ሰዓት ወልቂጤ ከተማ ከአዳማ ከተማ ይገናኛሉ፡፡
ወልቂጤ ከተማ በ10 ጨዋታ ሁለቱን አሸንፎ፣ በሁለቱ አቻ ወጥቶ እና በስድስቱ ተሸንፎ በ10 የግብ እዳ እና ስምንት ነጥብ በመያዝ ወራጅ ቀጣናው ላይ 13ኛ ነው፡፡ ሠራተኞቹ በመጨረሻው ሳምንት ጨዋታ በፋሲል ከነማ ቢሸነፉም እንቅስቃሴያቸው ግን ደካማ አልነበረም፡፡
ቡድኑ ከፍተኛ የኾነ ግብ የማስቆጠር ክፍተት አለበት፤ ለዚህም ነው በሦስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ያስቆጠረው፡፡ እናም በዛሬው ጨዋታ ይህን ችግር ቀርፎ ወደ ሜዳ መግባት ይጠበቅበታል። አሠልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት “የአጨራረስ ችግራችን መሻሻል አለበት” ብለዋል፡፡
ለወልቂጤ ተስፋዬ መላኩ ከአራት ጨዋታዎች ቅጣት በኋላ ዛሬ ይሰለፋል፡፡ አዳማ ከተማ በ10 ጨዋታ በሦስቱ በማሸነፍ፣ በአምስቱ አቻ በመውጣት እና በሁለት ጨዋታ በመሸነፍ በአንድ ንጹህ የግብ ክፍያ 14 ነጥብ በመያዝ 9ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ቡድኑ ኢትዮጵያ ቡናን ካሸነፈበት የስድስተኛው ሳምንት ጨዋታ በኋላ ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም፡፡ ስለዚህ ቡድኑ በማጥቃቱ በኩል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተቀዛቀዘ መጥቷል ማለት ይቻላል፡፡ አሠልጣኝ ይታገሱ እንዳለ በዛሬው ጨዋታ የቡድኑን የፊት መስመር አስተካክለው መቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ለእረፍት ወደ ሀገሩ ሄዶ የነበረው ቻርልስ ሪባኑ መመለሱን ተከትሎ አዳማ ከተማ በዛሬው ጨዋታ በሙሉ ሥብሥቡ ተዘጋጅቶ የሚቀርብ ይኾናል። ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ስድስት ጊዜ ተገናኝተዋል፡፡ አንድ- አንድ ጊዜ ሲሸናነፉ አራቱን ጨዋታዎች በተመሳሳይ 1ለ1 አጠናቀዋል። አዳማ ሰባት፣ ወልቂጤ ስድስት ግቦችን አስቆጥረዋል።
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!