ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የትምህርት ቤቶች የስፖርት ውድድር ተጠናክሮ እንዲቀጥል በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ተካሂዷል፡፡ በውይይቱ የተገኙት በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት መሠረተ ልማትና አገልግሎት ዴስክ ኀላፊ ታየ ግርማ የትምህርት ቤቶች ስፖርታዊ ውድድርን ማጠናከር ሳይቻል ሀገራዊ የስፖርት ውጤት መጠበቅ አይቻልም ብለዋል፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ተቋርጦ የነበረው የትምህርት ቤቶች ስፖርታዊ ውድድር በዘንድሮው የትምህርት ዘመን በዘጠኝ ቀጣናዎች ተደራጅቶ እየተከናወነ መኾኑንም ገልጸዋል።
በባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር የውድድር ስፖርቶች ክትትልና ድጋፍ ዴስክ ኀላፊ ዳንኤል ዳርጌ የትምህርት ቤቶች ስፖርታዊ ውድድር የተፈጠረውን ሀገራዊ የስፖርታዊ ውጤት መቀዛቀዝ ክፍተት ለመሙላት ሚናው ከፍተኛ መኾኑን ተናግረዋል። የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ለትምህርት ቤቶች ስፖርታዊ ውድድሮች ትኩረት በመስጠት ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ በመፈራረም ወደ ሥራ መግባቱንም አመላክተዋል፡፡ የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።
በትምህርት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ቦጋለ ስፖርቱ በማኅበረሰቡ ድጋፍ እንዲያገኝ መሥራት እንደሚጠበቅ አመካክተዋል፡፡ ከትምህርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በዘጠኙም ቀጣናዎች የተደለደሉ ሁሉም ክልሎች የአፈጻጸም ሪፖርት አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል፡፡ ከአንዳንድ ቀጣናዎች በስተቀር የስፖርት ሊጉን ስኬታማ ለማድረግ የአመራር ሚና በሚፈለገው ልክ አለመኾኑ ተመላክተዋል፡፡ ለትምህርት ቤት ስፖርት ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚገባም ተገልጿል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ኘ👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!