የሲቲ የቁልቁለት ጉዞ

0
216

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በስፔን ካታሎን የነገሡት፣ በጀርመን ሙኒክ የተዋቡት፣ በእንግሊዝ ማንቸስተር በከፍታ የታዩት፣ በድል ላይ ድል የለመዱት፣ ከክብር ላይ ክብር የደራረቡት፣ ማሸነፍን ባሕሪያቸው ያደረጉት፣ የድል ሽልማቶችን የሠበሠቡት ናቸው ፔፕ ጋርዲዮላ።

ነገር ግን አሁን ፔፕ እና ሲቲ ሌላ ታሪክ ላይ ናቸው። የእግር ኳስ ሊቁ ፔፕ ጋርዲዮላ በአሠልጣኝነት ዘመናቸው መላ ቅጡ የጠፋባቸው ዘመን ላይ ደርሰዋል፡፡ ድል የለመዱት አሠልጣኝ ከድል ጋር ተራርቀዋል፡፡ በሜዳቸውም፣ ከሜዳቸውም ውጭም እጅ እየሰጡ መመለስ ከጀመሩ ውለው አድረዋል፡፡

ጠንካራው ማንቸስተር ሲቲም በትንሹም በትልቁም የሚሸነፍ ቡድን ኾኗል። በባርሴሎና ቤት የዓለም ከዋክብትን እያሠለጠኑ በስኬት የተቆናጠጡት አሠልጣኝ፣ ወደ ጀርመን ተጉዘው በባየር ሙኒክም የዓለም ከዋክብትን እየመሩ ስኬት ደራርበዋል፡፡ ከጀርመን ወደ እንግሊዝ መጥተው በእንግሊዝ እግር ኳስ ኃያል ያልነበረውን ማንቸስተር ሲቲን አይነኬ አድርገዋል፡፡ በአውሮፓ እግር ኳስ አዲስ ታሪክ እንዲጽፍ አድርገውታል፡፡

ማንቸስተር ሲቲ በፔፕ ጋርዲዮላ ከተያዘ በኋላ የእንግሊዝ ሊግ የማይነካ ቡድን ኾኖ ለዓመታት ቆይቷል፡፡ ደግሞ ደጋግሞ የሀገር ውስጥ ዋንጫዎችን ወስዷል፡፡ በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ታሪክ ለአራት ተከታታይ ዓመታት የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ከፍ በማድረግ በታሪክ የመጀመሪያው ክለብ ኾኗል፡፡

ክፋቱ ግን ታሪክ በሠራበት ማግስት የቁልቁለት ጉዞ ላይ መገኘቱ ነው፡፡ የድል ዓመታት ተቀይረው የሽንፈት ጊዜያት መጥተዋል፡፡ ዘ ኢንዲያን ኤክስፕሬስ የተባለው ድረ ገጽ ፔፕ ጋርዲዬላ በዘመናቸው ገጥሟቸው የማያውቅ ቀውስ ውስጥ ናቸው ይላል፡፡ እርሳቸው በሲቲ ቤት ከአሠልጣኝ በላይ ናቸው የሚለው ዘ ኢንዲያን ኤክስፕረስ የማንቸስተር ሲቲ ደጋፊዎች የደከመውን የፔፕ ጋርዲዮላን መንፈስ ለመመለስ እየሞከሩ ነው ብሏል፡፡

ገንዘብ በአሁኑ ጊዜ በማንቸስተር ሲቲ ዙሪያ ያለውን ችግር ማስተካከል አይችልም የሚለው ድረ ገጹ የሲቲ የልብ ምት እና የባሎንዶር አሸናፊው ሮድሪ እና ሌሎች ወሳኝ ተጫዋቾች በቡድኑ ውስጥ አለመኖራቸው የሲቲን ሕይወት የከበደ አድርጎታል ነው የሚለው፡፡ ድልን ባሕሪያቸው አድርገው ለዓመታት የዘለቁት ፔፕ ጋርዲዮላ “ማሸነፍ አለብን። እኔ አሠልጣኝ ነኝ፡፡ መፍትሔዎችን መፈለግ አለብኝ ይበሉ እንጅ እስካሁን መፍትሔ አላገኙም። ይልቁንም የሽንፈት ምጣኔያቸው እየሰፋ እና እየጨመረ ሄደ እንጂ፡፡

ከጨዋታ በፊት እና ከጨዋታ በኋላ ከፊታቸው የሚቀርቡ ጋዜጠኞች የሚያነሱላቸው ጥያቄ ሃሳብ ጨርሰዋል ወይ? የሚል ኾኗል፡፡ ለምን ቢሉ እርሳቸው በአንድ ጨዋታ ሽንፈት ሲገጥማቸው በቀጣዩ ጨዋታ አስፈሪ ኾነው የሚመጡበት ለዓመታት የዘለቀ ለእርሳቸው ብቻ የተሰጠ የሚመስል ጥበብ ነበራቸውና፡፡

የእርሳቸው መልስም ደግም ወደ ከፍታችን ለመመለስ ጥረት እናደርጋለን ነው፡፡ በሁሉም ውድድሮች ካደረጓቸው 12 ጨዋታዎች በዘጠኙ የተሸነፉት አሠልጣኙ ይዋል ይደር እንጂ በራስ መተማመናችንን መልሰን ማግኘታችን አይቀርም ማለታቸውን ቢ ሶከር ዘግቧል፡፡

ግብ አዳኛቸው ኤርሊን ሃላንድ የግብ መስመሩ ጠፍቶበታል፡፡ ኳስ ከእግራቸው ጋር የተሰፋ የሚመስሉት የፔፕ ልጆች የቀደመ ብቃታቸውን እና ለዛቸውን አጥተዋል፡፡ ተደጋጋሚ ሽንፈቶች የተከበረውን የአሠልጣኝነት ዘመናቸውን እያከፋው ያለው ፔፕ ጋርዲዮላ የእርሳቸውን እና የተጫዋቾቻቸው በራስ የመተማመን ስሜታቸውን መልሰው ማግኘት እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡

“ደረጃ በደረጃ እንመለሳለን፡፡ በቡድኑ ውስጥ ጥሩ ስብዕናዎች አሉን፡፡ ፈጥኖም ይሁን ዘግይቶ መመለሳችን አይቀርም” የሚል ተደጋጋሚ ሃሳብ ይሰጣሉ። ካለፉት ስድስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ያስቆጠረው ሃላንድ አሁን እያደረጉት ያለው በቂ አለመኾኑን ተናግሯል፡፡ አሁን እያሳዩት ባለው አቋምም መከፋቱን ገልጿል፡፡ “መጀመሪያ ራሴን ነው የማየው፡፡ በቂ ነገር እያደረኩ አይደለም፡፡ ጠንክሬ መሥራት እና የተሻለ ማድረግ አለብኝ” ብሏል፡፡

በአሠልጣኝ ጋርዲዮላ እምነት እንዳለው የተናገረው ሃላንድ ፔፕ ጋርዲዮላ በሰባት ዓመታት ውስጥ ሥድስት ጊዜ የፕሪምየር ሊግ ዋንጫዎችን አሸንፈዋል፡፡ ስለዚህ ያንን መቼም አንረሳውም፡፡ መፍትሔዎችን ይፈልጋሉ። በየዓመቱ ያንን ሲያደርጉ ቆይተዋል። አሁንም እናምናለን ያደርጉታል፡፡ አሁን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ጠንክረን መሥራት አለብን ነው ያለው፡፡

ቢቢሲ በትንታኔው ፔፕ ጋርዲዮላ የማንቸስተር ሲቲን ችግር መፍታት አልተቻላቸውም ብሏል፡፡ በሲቲ ቤት 18 ዋንጫዎችን የሰበሰቡት አሠልጣኙ እንደ ማንኛውም አሠልጣኝ ሥራቸውን ሊያጡ ይችላሉ ይላል ቢቢሲ፡፡ ይህ ደግሞ ለእርሳቸው ታሪክ የማይመጥን እና አዲስ ነው፡፡ ፔፕ እንስተካከላለን ባሉበት ጊዜ ማስተካከል አልቻሉም፡፡ ድል የለመዱ የማንቸስተር ሲቲ ደጋፊዎች ደግሞ ጫናውን እያበዙባቸው ነው፡፡ በቶሎ ማስተካከል ካልቻሉ እና በቁልቁል ጉዟቸው ከቀጠሉበት መሰናበታቸው የሚቀር አይመስልም፡፡

ፔፕ ጋርዲዮላ በቡድናቸው ምን ሊፈጠር እንደሚችል እርግጠኛ አይደሉም፡፡ ባለፉት ዓመታት ድል የለመደው ቡድናቸው በዚህ ልክ ሲወርድ እና ከተፎካከሪነት ሲንሸራተት ምን ማድረግ እንዳለባቸው እያወቁ አይደለም ነው የሚለው፡፡ በእንግሊዝ እግር ኳስ ትልቅ ስም የገነቡት፤ ከሰር አሌክስ ፈርጉሰን በኋላ በእንግሊዝ እግር ኳስ አቢዮተኛ ኾነው የመጡት፣ የከተማ ተቀናቃኛቸውን ማንቸስተር ዩናይትድን እና ሌሎች የእንግሊዝ ቡድኖችን ደጋግመው ድል የነሱት እና በዋንጫ ያሸበረቁት ፔፕ አሁን ላይ ጀምበራቸው እያዘቀዘቀች፣ የከፍታ ዘመናቸው እያለፈች ይመስላል፡፡

የእግር ኳስ ተንታኞች ፔፕ ጋርዲዮላ ምን አልባትም በማንቸስተር ሲቲ መልበሻ ክፍል ውስጥ ያላቸው ተቀባይነት ቀንሷል፣ ክብራቸውንም ሳያጡ አይቀርም ይላሉ፡፡ ሚረር ስፖርት ደግሞ በአሠልጣኝነት ዘመናቸው ከባዱን ጊዜ እያሳለፉ በሚገኙበት በዚህ ወቅት በመልበሻ ክፍል ያላቸውን ተቀባይነት እንዳላጡ ተናግረዋል ብሏል፡፡ ነገር ግን የተጨዋቾች የቀድሞ መነሳሳት እና እስከ ሽርፍራፊ ሰከንዶች ድረስ ለክብር መፋለም እየታየ አይደለም፡፡

ሜል ኦን ላይን ፔፕ ጋርዲዮላ በጭንቀት ውስጥ መኾናቸውን ጽፏል፡፡ እርሷቸው የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ እንቅልፍ ማጣት እና ሌሎች የሚረብሿቸው ስሜቶች እየገጠሟቸው መኾንን አንስቷል፡፡ ጋርዲዮላ ባለፉት ዓመታት በከፍታ ላይ ነበሩ የሚለው ሜል አሁን ላይ ግን ያን ግርማቸውን እና ከፍታቸው እንደከዳቸው አንስቷል፡፡

በጭንቀት ውስጥ የሚገኙት አሠልጣኙ በአደባባይ ፊታቸው ሲቧጭሩ እየታዩ ነው፡፡ ሜል ኦን ላይን እንደሚለው ፔፕ ጋርዲዮላ ባለፉት ዓመታት ያሰኳቸው ስኬቶች አሁን ላይ ከትችት አያድኗቸውም፡፡ ምን አልባትም ከሥራቸው ሊሰናበቱ ይችላሉ፡፡ ፔፕ ጋርዲዮላ የእግር ኳስ ጥበባቸውን ተጠቅመው ማንቸስተር ሲቲን ወደ ከፍታው ይመልሱታል ወይስ ከፍ ባሉበት ቤት አንገታቸውን ደፍተው ይለቃሉ የሚለው ይጠበቃል፡፡

ክለባቸውን ወደ ክብሩ መልሰው አሁን ካሉበት ችግር ከወጡ እንደቀድሞው ሁሉ አድናቆት ይጎርፍላቸዋል፡፡ ይህ ሳይኾን ቀርቶ አቃተኝ ብለው ከተሰናበቱ ግን በፔፕ ጋርዲዮላ የአሠልጣኝነት ዘመን ውስጥ አዲስ ታሪክ ኾኖ ይመዘገባል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here