ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጥር የተጫዋቾች ዝውውር የሚከፈትበት ጊዜ መቃረቡን ተከትሎ የዝውውር ወሬዎች መሰማት ጀምረዋል። የማንቸስር ዩናይትዱ ማርከስ ራሽፎርድ በብዙ ክለቦች ዐይን ውስጥ ገብቷል። በአሠልጣኙ አሞሪም ተመራጭነትን ያጣው ራሽፎርድን የሳዑዲ ክለቦች ለማስፈረም እንቅስቃሴ ላይ መኾናቸውን ቴሌግራፍ አስነብቧል።
በተመሳሳይ የስፔኑ አትሌቲኮ ማድሪድ ራሽፎርድን በውሰት ለመውሰድ ፍላጎት አለው ተብሏል። ተጫዋቹ በማንቸስተር ደርቢ ከሥብሥቡ ውጭ ነበር። በተመሳሳይ ዛሬ ማንቸስተር ዩናይትድ ከቶትንሃም ጋር በሚያደርገው የካራቦ ጨዋታ ራሽፎርድ ከሥብሥቡ ውጭ ኾኗል። ማንቸስተር ሲቲ ማርክ ጉሂን ለማስፈረም ፍላጎት አለው። በውጤት ቀውስ ውስጥ የሚገኘው ማንቸስተር ሲቲ በጥር ዝውውር ተጫዋቾችን እንደሚያስፈርም ይጠበቃል።
በርካታ ጎሎች እየተቆጠሩበት ያለው የተከላካይ ክፍልን ለማጠናከር የጋርዲዮላ ምርጫ የፓላሱ ጉሂ መኾኑን ፉትቦል ኢንሳይደር አስነብቧል። ሲቲ በተመሳሳይ ከብራይተን ኢቫን ፈርጉሰንን ለማስፈረም ፍላጎት አለው። ሪያል ማድሪድ ትረንት አርኖልድን ከሊቨርፑል በማስፈረም ሃሳቡ ቀጥሏል። ነገርግን ሊቨርፑል የአርኖልድን ውል ለማራዘም እየሠራ እንደሚገኝ የቢቢሲ መረጃ ያሳያል።
ማንቸስተር ዩናይትድ ኑኖ ሜንዴዝን ለማስፈረም ማሰቡን ደግሞ ስካይ ስፖርት ጽፏል። ፖርቱጋላዊ ሜንዴዝ አሁን ለፒኤስጅ እየተጫወተም ይገኛል። ኦሎምፒክ ማርሴይ ፖል ፖግባን ለማስፈረም እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ ጎል አስነብቧል። ፖግ ከቅጣት መልስ ከጁቬንተስ ጋር ተለያይቶ አዲስ ክለብ እየፈለገ ይገኛል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!