የአፍሪካ ጅምናስቲክ ፌዴሬሽን ሥራ አሥፈፃሚ አባል እና ሁለገቡ የስፖርት ሰው

0
234

አዲስ አበባ: ታኅሣሥ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ባሕርዳር ከተማ ተወልደው ያደጉት አቶ ገበያው ታከለ በተለያዩ ዘርፎች በስፖርቱ 30 ዓመታትን የተሻገረ ተሳትፎ አላቸው። በልጅነታቸው በውኃ ዋና፣ በብስክሌት እና በእግር ኳስ ውድድሮች ይሳተፉ እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ ገበያው በተለይ ለእግርኳስ ስፖርት የተለየ ፍቅር እንደነበራቸው እና ስታዲየም ውስጥ ቋሚ መቀመጫ እንደነበራቸው ያስታውሳሉ።

አቶ ገበያው ክለቤ ነው ለሚሉት ቅዱስጊዮርጊስ በ1970ዎቹ መጨረሻ እና በ1980ዎቹ መጀመሪያ ከድጋፍ ባለፈ በወቅቱ ለክለቡ ውጤታማነት የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ገልጸዋል። በስፖርቱ ከ30 ዓመት በላይ ተሳትፎ ያላቸው አቶ ገበያው ለተለያዩ ስፖርቶች እና ውድድሮች ድጋፍ በተጠየቁ ቁጥር የሚችሉትን እገዛ ሲያደርጉ መኖራቸውንም ያነሳሉ።

አቶ ገበያው አኹን በፌደሬሽን ፕሬዚዳንትነት በሚመሩት ጅምናስቲክ ስፖርትም ከ20 ዓመታት በላይ በስፖርት መሪነት የቆዩ ሲኾን ለጅምናስቲክ ስፖርት ዕድገትም ዕውቀት እና ገንዘባቸውን እየሰጡ ይገኛሉ። የኢንተርናሽናል ጅምናስቲክ ፌዴሬሽን ኮንግረስ በጥቅምት ወር በኳታር ዶሃ ባደረገው ጉባኤ ደግሞ አቶ ገበያው ታከለ ከፍተኛ ድምጽ በማግኘት የካውንስሉ አባል ኾነው ተመርጠዋል።

በቅርቡ የአፍሪካ ጅምናስቲክ ፌዴሬሽን በግብጽ ካይሮ ጉባኤውን ሲያደርግም የአፍሪካ ጅምናስቲክ ፌዴሬሽን የሥራ አሥፈፃሚ አባል ኾነዋል። ከአፍሪካ ጅምናቲክ ፌዴሬሽን ሰባቱ ሥራ አሥፈፃሚዎች መካከል አንዱ ኾነው የተመረጡት አቶ ገበያው ይህን ኀላፊነት በማግኘታቸው ደስተኛ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡ በተለይ ለሀገራቸው የስፖርት ዕድገት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖራቸው ለአሚኮ ተናግረዋል።

በአህጉሩ የጅምናስቲክ ስፖርት ላይ ቀጥተኛ ውሳኔ ሰጭ መኾን ፋይዳው የጎላ መኾኑን የሚገልጹት የኢትዮጵያ ጅምናስቲክ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንቱ ይህ ዕድል ለሌሎች ፌዴሬሽኖችም ትልቅ መነቃቃት እንደሚፈጥር ተናግረዋል። ክቡር ይድነቃቸው ተሰማ በአህጉር እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በእግር ኳሱ የነበራቸውን የመሪነት ሚና ያስታወሱት አቶ ገበያው ተመሳሳይ ውክልናዎችን ለማግኘት፣ ተጽዕኖም ለመፍጠር ፌዴሬሽኖች ራሳቸውን ማጠናከር እና መንግሥትም አስፈላጊውን ድጋፍ እና ክትትል መስጠት እንዳለበት አንስተዋል።

አቶ ገበያው ታከለ በጅምናስቲክ ፌዴሬሽን ካላቸው ኀላፊነት በተጨማሪ በኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴም ረዘም ያለ የመሪነት ጊዜን አሳልፈዋል። በቆይታቸው ስፖርቱን እና አትሌቶችን በመደገፍም ይታወቃሉ። ከአትላንታ እስከ ሪዮ በንዑስ እና በዋና ቡድን መሪነት በርካታ ኦሎምፒኮችን መርተዋል። በእነዚህ ጊዜያትም አይረሴ ትዝታዎችን እንዳሳለፉ ይናገራሉ።

ኦሎምፒክ ላይ በነበራቸው ድጋፍ እና አስተዋጽኦ መነሻም ዛሬ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የክብር አባል ናቸው። አቶ ገበያው ታከለ በስፖርቱ ያሳለፉትን ጊዜ እና ትዝታ፣ የወደፊት ዕቅዳቸውን በተመለከተ ብሎም ስለ ኢትዮጵያ ስፖርት ያላቸውን ሰፊ ልምድ ያካፈሉበት ሙሉ ቆይታ በስፖርት ባለታሪኮቹ ፕሮግራም እሑድ ቀን 7:00 ሰዓት በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ይቀርባል።

ዘጋቢ፡- ባዘዘው መኮንን

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here